Diaspora Profile Documents Diaspora Profile Documents
Minimize Maximize

"በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ መምህር ዶክተር ኃይሌ ክብረት፤በኢትዮጵያ ልማት ምርምር ኢንስቲትዩት ተመራማሪ ዶክተር በሪሁ ተቀዳ፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሶሾሎጂ ትምህርት ክፍል መምህር ዶክተር የራስወርቅ አድማሱ እንዲሁም የሚሉት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የዳያስፖራ መረጃና ጥናት ዳይሬክተር አቶ መሃመድ በሪሁ ስለ ዳያስፖራው በጋራ ባደረጉት ውይይት ላይ እንደገለጹት ከሁለት እስከ ሦስት ሚሊዮን የሚጠጉ የኢትዮጵያ ዳያስፖራዎች በተለያዩ አገራት እንደሚገኙ መረጃዎች ያመለክታሉ። ዳያስፖራው በተለያዩ የልማት ዘርፎች በመሳተፍ በአገሪቱ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ላይ ከፍተኛ ሚና የመጫወት አቅም አለው፡፡ ሆኖም ግን የዳያስፖራው ተሳትፎና ውጤቱ የሚፈለገው ደረጃ ላይ አልደረሰም፡፡ ኢትዮጵያ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዳያስፖራዎች ቢኖሯትም ይህን ኃይል በአገሪቱ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ላይ በማሳተፍ ረገድ የተሰራው ሥራ በጣም አነስተኛ ነው ይላሉ። አብዛኛው የኢትዮጵያ ዳያስፖራ በሰሜን አሜሪካ፣ አውሮፓ እና መካከለኛው ምስራቅ አገራት የሚገኙ ሲሆን በእነዚህ አገራት ማግኘት ከሚቻለው ከፍተኛ ካፒታል፣ የቴክኖሎጂና የእውቀት ሽግግር አንፃር ሲመዘን የዳያስፖራው አገራዊ እንቅስቃሴ ውስን መሆኑን ይገልጻሉ፡፡ የአገሪቱ ዳያስፖራ ደረጃው ቢለያይም በኢኮኖሚው ላይ የራሱን ሚና እየተጫወተ መሆኑን ያነሳሉ። ዳያስፖራው ለዘመድና ለቤተሰብ በሚልከው ገንዘብ ለውጭ ምንዛሪ ግኝት የበኩሉን አስተዋፅኦ እያበረከተ መሆኑን በማሳያነት ያቀርባሉ፡፡ አገሪቱ ከወጪ ንግድ ከምታገኘው የውጭ ምንዛሪ የሚበልጥበት አጋጣሚዎች መኖሩ ጠቁመው ተሳትፎው ከህንድ፣ ቻይና፣ ፊሊፒንስና እስራኤል ጋር ሲነፃፀር ጉዳዩን ጥያቄ ምልክት ውስጥ ይከተዋል ባይ ናቸው፡፡ ወርልድ ባንክ በቅርቡ ባወጣው መረጃ 35 ሚሊዮን ያህል ስደተኛ ዜጋ ያላት ቻይና፤ እ.ኤ.አ በ2017 በአስራ አንድ ወራት ብቻ ዳያስፖራው ካደረገው የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት 122 ቢሊዮን ዶላር ካፒታል ተመዝግቧል። በተመሳሳይ ዓመት በተለያዩ የውጭ አገራት የሚገኙ የህንድ ዳያስፖራዎች 65 ቢሊዮን ዶላር ወደ አገራቸው ልከዋል፡፡ በ2009 ዓ.ም ኢትዮጵያውያን ዳያስፖራዎች በቀጥታ ኢንቨስትመንት ከ15 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ማስመዝገባቸው ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡ ለቤተሰቦቻቸው አራት ነጥብ ስድስት ቢሊዮን ዶላር በመላክም ለውጭ ምንዛሪ ግኝት የበኩላቸውን ሚና መጫወት ችለዋል፡፡ የዳያስፖራው የልማት ተሳትፎ በሚጠበቀው ደረጃ ላለማደጉ መንግሥት የቤት ሥራውን በትክክል ባለመስራቱ እንደሆነ ምሁራኑ ይገልፃሉ። በተለያዩ አገራት ባሉ ኢትዮጵያውያን ዘንድ የጋራ መግባባት መፍጠር እንደሚያስፈልግም ይጠቅሳሉ። ዳያስፖራው የተለያየ ፖለቲካዊ አስተሳሰብ ቢኖረውም የአስተሳሰብ ልዩነት በማጥበብ ያካበተውን ሀብት፣ዕውቀትና ልምድ በመጠቀም በአገሩ እንዲያለማ ጥረት ማድረግ እንደሚጠይቅ ተገልጿል፡፡ ዳያስፖራው በአገሩ የልማት እንቅስቃሴ ላይ ያለው ሚና ዝቅተኛ ለመሆኑ ምክንያቱ ራሱ ዳያስፖራው የትውልድ አገሩ ጉዳይ የራሱ ጉዳይ መሆኑን በመገንዘብ የሚያደርገውን ተሳትፎ በሚፈለገው ደረጃ አለመሆኑን ይገልፃሉ፡፡ ለዚህም የሌሎች አገራት ዳያስፖራዎችን ተሳትፎ በማነፃጸሪያነት ያቀርባሉ ፡፡ የህንድና የቻይና ዳያስፖራዎች ከአገራቸው ውጭ ተሰማርተው ሲሰሩ አገራቸውን ማልማት እንዳለባቸው ትኩረት ይሰጣሉ፡፡ በዚህም በአገራቸው ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ላይ ትልቅ አስተዋፅዖ አበርክተዋል፡፡ በዚህ በኩል የኢትዮጵያ ዳያስፖራዎች የሚጠበቅባቸውን የነቃ ተሳትፎ እንዲኖራቸው ብዙ ሥራ ማከናወን ይገባል ይላሉ፡፡ ከገንዘብ ፣ከዕውቀት፣ ጠንክሮ ከመስራት እና አገርን ለመለወጥ በምን ዓይነት መንገድ መሳተፍ እንደሚገባ ከመረዳት አንፃር በዳያስፖራው በኩል ክፍተት አለ፡፡ ይህ ክፍተት የዳያስፖራው ተሳትፎ በሚፈለገው ደረጃ እንዳይጓዝ አድርጎታል፡፡ ወደ አገራቸው በመምጣት በተለያዩ ዘርፎች ለሚሳተፉ ዳያስፖራዎች የሚሰጠው አገልግሎት ቀልጣፋ አለመሆንና መሰል ችግር የተሳትፎውን ደረጃ ከመጉዳቱም በላይ ወደ አገራቸው መምጣት የሚፈልጉ ዳያስፖራዎችን ተነሳሽነት አቀዛቅዞታል ይላሉ። የተለያዩ ፕሮጀክቶችን በመቅረጽ ወደ ተግባር የገቡ ዳያስፖራዎች ቁጥር ቀላል አለመሆኑን ጠቁመው የመልካም አስተዳደር እጥረትና ሙስና አሉታዊ ተፅዕኖ ማሳደሩን አስገንዝበዋል፡፡ «በየጊዜው ከዳያስፖራው ጋር የተለያዩ ውይይቶች ተደርገዋል፡፡ ይህም የዳያስፖራው የልማት ተሳትፎ እንዲጨምር አግዟል» ይህም ሆኖ ግን የዳያስፖራው ተሳትፎ የሚፈለገው ደረጃ አለመድረሱን ይስማማሉ፡፡ ለውጤታማነቱ ውስንነት በዳያስፖራው በኩል የሚነሱ ችግሮች መኖራቸውን ምሁራኑ ይጠቁማሉ፡፡ በተሰጣቸው የኢንቨስትመንት ቦታ ላይ ለማልማት የአቅም ማነስ፣ የተቀበሉትን ቦታ ለሌላ አካል ለማስተላለፍ መሞከር፤ ፈጥኖ ወደ ሥራ አለመግባትና አጥሮ ማስቀመጥን የመሳሰሉ ክፍተቶች ይስተዋላሉ። ዳያስፖራው በራሱ ተነሳሽነት ለአገሩ ልማትና ዕድገት የበኩሉን ለማበርከት መንቀሳቀስ እንዳለበትም ያስገነዝባሉ፡፡ «ዳያስፖራውን በተለያዩ ዘርፎች በማሳተፍ በአገሩ ኢኮኖሚ ላይ አሻራውን እንዲያሳርፍ ማነሳሳት የሚያስችል ተግባር ውስንነት ያለው መሆኑ» በኢትዮጵያ ውስጥ የሚከናወኑ ተግባራትን በተመለከተ ወቅታዊና ትክክለኛ መረጃዎችን የሚያገኝበት አጋጣሚ ውስን መሆን፡፡ የዳያስፖራውን የልማት ተሳትፎ በሚፈለገው ደረጃ ለማሳደግ መሰራት ያለባቸው የቤት ሥራዎች እንዳሉ ያምናሉ፡፡ በመሆኑም ዳያስፖራው ስለ አገሩ ትክክለኛ መረጃና ፍቅር ኖሮት እንዲሳተፍ መንግሥት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ይገልፃሉ። ምሁራኖቹ እንደገለጹት የተፈለገውን ውጤት ለማምጣት ተከታታይነት ያለው በጥናትና ማስረጃ የተደገፈ ቅስቀሳ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ቢሮክራሲውን መፍታትና የተቀላጠፍ አገልግሎት መስጠት ይገባል፡፡ የዳያስፖራውን ተሳትፎ ለማሳደግ ቀደም ባሉት ዓመታት የተጀመሩት ተግባራት ተጠናክረው መቀጠል አለባቸው፡፡ የወጡትን ፖሊሲዎች በአግባቡ መተግበር፣ ይህን ለማስፈፀም የተቋቋሙ ተቋማትም ኃላፊነታቸውን በብቃት መወጣት ይጠበቅባቸዋል፡፡ በተለያዩ ዘርፎች የተሰማሩ ዳያስፖራዎች የሚያነሷቸውን ቅሬታዎች መፍታት ለሚፈለገው ውጤት ስኬት ወሳኝ መሆኑን ምሁራኑ ያስገነዝባሉ፡፡ በዚህ በኩል የሚስተዋሉ ክፍተቶችን ማጥበብና ችግሮችን መፍታት ሌሎች ዳያስፖራዎች ወደ አገር መጥተው እንዲያለሙ ከፍተኛ መነቃቃትን ይፈጥራል፡፡ በዚህ በኩል የሚታዩ ክፍተቶችን ማስተካከል ከተቻለ የተሻለ ውጤት ይመዘግባል የሚል እምነት አላቸው፡፡ስለሆነም መንግሥት በዚህ በትኩረት መስራት ይኖርበታል፡፡ የተጠቀሱትን ችግሮች መፍታት ካልተቻለ ዳያስፖራው ራሱን ተጠቃሚ ሆኖ አገሪቱ ከዳያስፖራው ማግኘት የሚገባትን ጥቅም ታጣለች ይላሉ ምሁራኑ፡፡ ዳያስፖራው እንደነ ቻይና፣ ህንድ፣ እስራኤልና ፊሊፒንስ በአገሪቱ ምጣኔ ሃብት ላይ መጫወት የሚገባውን ሚና እንዲኖረው እና ወደ አገር ውስጥ መጥቶ የሚያለማው እየጨመረ እንዲሄድ ለማስቻል ከፍተኛ ጥረት ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ በዚህም አገሪቱ በተለያዩ ጊዜያት በኢንቨስትመንት ፣በውጭ ምንዛሪ፣በዕውቀትና በቴክኖሎጂ ሽግግር ከዳያስፖራው የምታገኘውን ከፍተኛ ጥቅም ታረጋግጣለች፡፡" ምንጭ – አዲስ ዘመን