
መስከረም 14, 2024
የቤቶች ልማት መሪ ስራ አስፈጻሚ በበጀት ዓመቱ እቅድ አፈጻጸም እና በ2017 በጀት ዓመት እቅድ ላይ ውይይት አካሄደ
አዳማ፣ነሐሴ 10 ቀን 2016 ዓ/ም (ከመልሚ)
በከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር የቤቶች ልማት መሪ ስራ አስፈጻሚ የ2016 በጀት ዓመት እቅድ አፈጻጸም እና የ2017 በጀት ዓመት እቅድ ላይ ከመሪ ስራ አስፈፃሚው አመራሮችና ባለሙያዎች ጋር በጋራ በመሆን በአዳማ ከተማ ውይይት አካሄዷል።
የውይይት መድረኩ የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱን የ10 ዓመት እና የ3 ዓመት የልማትና የኢንቨስትመንት እቅድ መነሻ በማድረግ የቤቶች ልማት መሪ ስራ አስፈጻሚ የ2016 በጀት አመት እቅድ አፈጻጸም እና የ2017 በጀት አመት እቅድ እንዲሁም የሪል ስቴት፣ የማይንቀሳቀስ የንብረት ግብይት እና ግመታ ረቂቅ አዋጅን መሰረት ያደረገ ነው።
በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በቤቶች ልማት መሪ ስራ አስፈጻሚ የቤት አቅርቦት እና የፋይናንስ ማሻሻያ ዴስክ ኃላፊ በወ/ሮ ሙሉእመቤት ከበደ እንደ ተገለጸው የቤት ልማትና አቅርቦትን በማሻሻል እያደገ የመጣውን ተጨማሪ የቤት ፍላጎት በበቂ ሁኔታ ለማስተናገድ የሚያስችል ስርዓት እና አቅም በመፍጠር ሁሉንም አቅሞች በመጠቀም ለሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች በቂ የመኖሪያ ቤት በዘላቂነት ተደራሽ ለማድረግ ዓላማ በማድረግ እየተሰራ እንደሆነ ተናግረዋል።
ከዚህ ጋር ተያይዞ በበጀት አመቱ የቤቶች ልማትን አስመልክቶ በክልል ከተሞች እና በገጠር ማዕከላት የቤት ልማት በትኩረት የተዳሰሰ ሲሆን በቀጣይ ዓመትም ስራዎቻችንን በማጠናከር የምንሰራ ይሆናል ብለዋል።
የቤቶች ልማት ጥናት እና የግል ሴክተር ተሳትፎ ዴስክ ኃላፊው አቶ በየነ መለሰ በበኩላቸው የሪል ስቴት እና የማይንቀሳቀስ የንብረት ግብይት እና ግመታ አዋጅን ሲያቀርቡ እንደተናገሩት ይህ ረቂቅ አዋጅ በሚኒስቴሮች ምክር ቤት ጸድቆ በቀጣይ በተወካዮች ምክር ቤት የሚጸድቅ ሲሆን የአዋጁ አስፈላጊነት ከሪል ስቴት ልማት ጋር የተያያዘ አሰራርን በመቀየር የሪል ስቴት ኢንቨስትመንት ማበረታታትና የቤት አቅርቦት እንዲሻሻል በማስፈለጉ ነው ብለዋል።
የማይንቀሳቀስ ንብረት ግመታ ስርዓቱ ዘመናዊና ተገማች ዋጋ እንዲኖረው በማድረግ የከተሞች ልማት እንዲፋጠን ከመሠረተ ልማት ዝርጋታ ጋር ተያይዞ የሚመጣ የንብረት እሴት ጭማሪን መሰረት አድርጎ የከተሞች ገቢ ማስፋፋት በማስፈለጉ ነው በሚል አክለው ገልጸዋል።
ከተወያዮችም የተለያዩ አስተያየቶች እና ጥያቄዎች ተነስተው ከመድረክ ሀሳብ ተሰጥቶባቸዋል።
ሪፖርተር ኮከቤ ቢፍቱ
የካሜራ ባለሙያ አስመላሽ ተፈራ
Posted in: Uncategorized