ህዳር 20, 2025
ሠመራ፣ህዳር 10/2018 ዓ.ም (ከመልሚ):-
ከህዳር 6 ጀምሮ በሠመራ ሎጊያ ከተማ ሲከናወን የቆየው
10ኛው የኢትዮጵያ ከተሞች ፎረም በዛሬው እለት የኢፌድሪ ም/ጠቅላይ ሚኒስትር ክቡር አቶ ተመስገን ጥሩነህ፣ የአፋር ክልላዊ መንግስት ፕሬዝዳንት ክቡር ሀጂ አወል አርባ፣ የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትር ክብርት ወ/ሮ ጫልቱ ሳኒ እንዲሁም የተሳታፊ ከተሞች ተወካዮች በተገኙበት የመዝጊያ መርሀ ግብር ተካሄዷል።
በዚሁ ወቅት ክብርት ሚንስትር ወ/ሮ ጫልቱ ሳኒ እንደተናገሩት ከዋና ዋና የትኩረት መስኮች መካከል የአገልግሎት ዘርፉን ማዘመን ፤ የከተሞች ሴፍቲኔትና ምግብ ዋስትና፤ የቤት ልማት፤የአረንጔዴ መሠረተ-ልማትና የስራ ዕድል ፈጠራ፤ የከተማ መሬት፣ ፕላን እና የካዳስተር ስርዓትን ተግባራዊነት አውስተዋል።
ይህን በተመለከተ ሲገልጹም፡- ያለንበት ዘመን ዓለማችን ተዓምራዊ በሚመስል መልኩ በለውጥ ፍጥነት እየገሰገሰች ያለችበት፤ ከተማና ከተሜነትም የዚህ ለውጥ መነሻ፣ የከፍታውም መድረሻ ምልክት ሆነው የሚታዩበት ልዩ ጊዜ ነው፡፡
እኛም የሂደቱ አካል በመሆናችን ከለውጡ ጋር በእኩል ለመጓዝ በመንግሥት ደረጃ ትኩረት ሰጥተን፣ ፖሊሲ ቀርፀን፣ ግብ አስቀምጠን ስንሰራ ቆይተናል፤ አብነት የሚሆኑ ውጤቶችንም አስመዝገበናል።
ስለዚህ ስራችን ከህብረተሰቡ የዕለት ተዕለት ኑሮና ህይወት ጋር በእጅጉ የተሳሰረ ስለሆነና በቂ ትኩረትና ክትትልን ስለሚሻ የአገልግሎት ዘርፉን ማዘመን ልዩ ትኩረት እንደሚሻ ለመግለፅ እፈልጋለሁ ብለዋል።
የከተሞች ሴፍቲኔትና ምግብ ዋስትና ሥራን በተመለከተም በአሁኑ ወቅት ካለው የዋጋ ንረትና የኑሮ ውድነት አኳያ ከድህነት ወለል በታች ያሉ የከተማ ነዋሪዎችን በመደገፍ በኩል ትልቅ ሚና እየተጫወተ እንደሆነ ገልጸዋል።
ሌላው ትኩረት የሰጡት ጉዳይ የቤት ልማት ሲሆን የቤት ልማት አማራጮች እንዲሰፉና የግል አልሚዎች በስፋት እንዲሳተፉ በተጨማሪም፣ በማህበራት፣ በመንግስትና በባለሃብቶች ጥምረት እንዲሁም በሌሎች ሞዳሊቲዎች የመስራት አቅጣጫን አስቀምጦ ወደ ሥራ በመግባቱ ይበል የሚያሰኝ ውጤቶችን ማየት እንደተቻለ
ገልጸዋል።
የአረንጓዴ መሠረተ-ልማት ማስፋፋት ሥራዎችን በተመለከተም በትልቅ ስኬት የሚታዩ ሥራዎች የተሰሩ ሲሆን ከአረንጓዴ ልማት ስራዎች ጋር በተያያዘ ለዜጎች እየተፈጠረ ያለው የሥራ ዕድልና የአስተሳሰብ ለውጥም ነገን በላቀ ተስፋ እንድንመለከት የሚያደርግ ሆኗል ብለዋል።
ሌላው ከዋነኛ ሥራዎቻችን መካከል አንዱ የሆነው የከተማ መሬት አጠቃቀም ፕላን እና የመሬት ልማትና ካዳስተር ሥርዓታችንን በዘመናዊ የመረጃ ስርአት (ካዳስተር) በተደገፈ አግባብ በማስተዳደር የመሬት ሀብታችን ለሀገራችን ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ዕድገት የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲያበረክት የሚያስችሉ ሥራዎችን ማከናወን ነው፡፡
እንዲሁም የኮንስትራክሽን እንዱስትሪ ስራችንን ስንመለከትም ዓለም አቀፋዊ ተፅዕኖው እንዳለ ሆኖ በብዙ ውስብስብ ችግሮች ውስጥ ያለ ሴክተር ቢሆንም በዘርፉ ያሉ ችግሮችን ለመፍታትና ዘርፉን በተሻለ ለመምራት የሚያስችሉ በርካታ ስራዎች ተሰርተዋል ብለዋል።