
ህዳር 3, 2024
በከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር በረቂቅ ደረጃ ተዘጋጅተው እንዲፀድቁ ለሚኒስትሮች ም/ቤት እና ለህዝብ ተወካዮች ም/ቤት ተልከው ለተጨማሪ እይታ ለከተማ መሰረተ ልማትና ትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የተመሩ ረቂቅ አዋጆች ለቋሚ ኮሚቴው አባላት ገለፃና ማብራሪያ በመስጠት በጉዳዩ ላይ የጋራ መግባባት ለመፍጠር የተዘጋጀ የውይይት መድረክ ነው።
የውይይት መድረኩን ያስጀመሩት የከተማ መሠረተ ልማትና ትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ የተከበሩ እሸቱ ተመስገን (ደ/ር) እንደተናገሩት አዋጆቹ ላይ የጋራ ግንዛቤ መያዝ ያስፈለገው ከመጽደቁ በፊት ግልጽነት እንድፈጠር እና ለሚነሱት መሠረታዊ ጥያቄዎች ምላሽ በመስጠት ባጠረ ጊዜ አዋጆቹ ጸድቀው ወደ ስራ እንዲገቡ ለማስቻል ነው።
በ2017 በጀት ዓመት በረቂቅ ደረጃ ተዘጋጅተው እንዲፀድቁ ለሚኒስትሮች ም/ቤት እና ለህዝብ ተወካዮች ም/ቤት ተልከው ለተጨማሪ እይታ ለከተማ መሰረተ ልማትና ትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የተመሩት የኢትዮጵያ የህንጻ አዋጅ እና የሪል ስቴት ልማት እና የማይንቀሳቀስ ንብረት ግብይትና ግመታ አዋጅ እንድሁም የሊዝ አዋጅ እና የመሬት ይዞታ ምዝገባ አዋጆች ናቸው።
አዋጆቹ በዝርዝር ከቀረቡ በኋላ ከቋሚ ኮሚቴዎች በርካታ ሀሳቦች ተነስተዋል፡፡ አዋጆቹ እስከታችኛው መዋቅር ወረደው ተፈጻሚ እንዲሆኑ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የሚጫወተው ሚና ምን እንደሆነና የተሻሻሉት አዋጆች ከነባሮቹ አዋጆች የሚለዩበትን መንገድ በዝርዝር እንዲቀመጥ የቋሚ ኮሚቴው አባላት አንስተዋል ።
በመጨረሻም በሚኒሰቴር መስሪያ ቤቱ የበላይ አመራር እና የሚመለከታቸው የሥራ ኃላፊዎች ተገቢውን ማብራሪያና ምላሽ ሰጥተዋል፡፡