ህዳር 20, 2025
ሰመራ-ሎጊያ፣ ህዳር 10፣ 2018ዓ.ም (ከ.መ.ል.ሚ) ከህዳር 6 ቀን ጀምሮ ለተከታታይ አምስት ቀናት ሲካሄድ የነበረው 10ኛው የኢትዮጵያ ከተሞች ፎረም ተጠናቋል፡፡
10ኛው የኢትዬጵያ ከተሞች ፎረም በዛሬው እለት የኢፌዴሪ ም/ጠቅላይ ሚኒስትር ክቡር አቶ ተመስገን ጥሩነህ፣ የአፋር ክልላዊ መንግስት ፕሬዝደንት ክቡር ሀጂ አወል አርባ፣ የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትር ክብርት ወ/ሮ ጫልቱ ሳኒ ፣የፈደራል እና የክልል የስራ ሀላፊዎች፣ የጎረቤት ሀገራት ተወካዮች፣ የከተማ ከንቲባዎች፣ የልማት አጋሮች፣ የሀገር ሽማግሌዎችና የሀይማኖት አባቶች፣ እንዲሁም የተሳታፊ ከተሞች ተወካዬች በተገኙበት የመዝጊያ መርሀ ግብር ፍጻሜውን አግኝቷል።
ፎረሙ በተለያዩ መርህ- ግብሮች ታጅቦ በሰላም ለመጠናቀቅ የበቃው የክልሉ ሰላም ወዳድና የፍቅር ተምሳሌት የሆነው የአፋር ክልል ማህበረሰብና የጸጥታ ኃይሎች ባደረጉት ቅንጅታዊ አሰራር መሆኑን የገለጹት የአፋር ብሔራዊ ክልላዊ መንግሰት ርዕሰ-መስተዳደር ክቡር ሐጂ አወል አርባ በመዝጊያ ንግግራቸውና የ11ኛው የከተሞች ፎረም አዘጋጅ ከተማ ለሆነው ለአሶሳ ከተማ አርማውን ባስረከቡበት ወቅት ነው፡፡
የክልሉ ርዕሰ-መስተዳደር ክቡር ሀጂ አወል አርባ አያይዘውም በዚህ ታላቅ የከተሞች ፎረም በመካከላችሁ በመገኘቴ ታላቅ ኩራት እና ምስጋና ይሰማኘል ያሉት ክቡር ርዕሰ-መስተዳደሩ ለተከታታይ አምስት ቀናት በከተሞቻችን እድገት ዙሪያ በጋራ በመወያየት፣ በዋጋ የማይተመን ልምድ ተካፍለናል፤ ስለ ወደፊቱ የበለጸጉ የኢትዮጵያ ከተሞች ቀጣይነት አዳዲስ መንገዶችን ቀይሰናል ብለዋል።
ፎረሙ የከተሞች መስፋፋት ማለት ከተሞችን መገንባት ብቻ ሳይሆን አካታች፣ ጠንካራ እና የበለፀገ ማህበረሰብን መገንባት እንደሆነም በድጋሜ አረጋግጦልናል። የተቀናጀ እቅድ፣ ጠንካራ ተቋማት፣ ፈጠራ እና የዜጎች ተሳትፎ ካለ ተግዳሮቶችን እንዴት ወደ እድል መቀየር እንደሚቻል አሳይቶናል ብለዋል ርዕሰ-መስተዳደሩ።
10ኛው የኢትዮጵያ ከተሞች ፎረም ስኬቶቻችንን ከማክበር ባለፈ ከምንጊዜውም በላይ ትኩረት ልንሰጣቸው የሚገቡ ስራዎችን ትኩረት ሰጥተን በመስራት የህብረተሰባችንን የልማት ጥያቄዎችን ለመመለስ ከተለመደው የአሰራር ዘይቤ ወጥተን ሌት ተቀን ልንሠራ ይገባናል ብለዋል፡፡
ከዚህ ጋር በተያያዘ ፎረም በስኬት እንዲጠናቀቅ ላደረጉ የፌዴራል እና የክልል አመራሮች ፣ ቀጣይነት ያለው ድጋፋቸው ላልተለየን ዓለም አቀፍ አጋሮች እና የልማት ኤጀንሲዎች፤ እንዲሁም በሙያቸው እና በልምዳቸው ከተሞቻችንን ቅርጽ ለሚያሲዙልን ባለሙያዎች፤ የግሉ ሴክተር እና የሲቪክ ማኅበራት፤ ከሁሉም በላይ በድምጻቸው የሚመሩን መላው ዜጎች እና የማህበረሰብ ተወካዮች ያለኝን ታላቅ አድናቆት ለመግለጽ እወዳለሁ ብለዋል ክቡር ሀጂ አወል አርባ፡፡
ከ10ኛው የኢትዮጵያ ከተሞች ፎረም መጠናቀቅ ጋር ተያይዞ ወደ የመጣንበት ስንመለስ በመንግስት ደረጃ ያለውን ቅንጅት ለማጠናከር፣ ለከተማ ትራንስፎርሜሽን ፈጠራን እና ቴክኖሎጂን ለመጠቀም፣ ዜጎችን በተለይ ወጣቶችን፣ ሴቶችን እና ተጋላጭ የማህበረሰብ ክፍሎችን የፖሊሲዎቻችን ማዕከል ለማድረግ እና የመሳሰሉ ጉዳዮችን ወደ መሬት በማወረድ ለሚጠበቀው ግብ ስኬት የጋራ ርብርብ ማድረግ በየደረጃው ከሚገኝ አመራር እንደሚጠበቅ ርዕሰ-መስተዳደሩ ተናግረዋል፡፡
በመጨረሻም 10ኛውን የኢትዮጵያ የከተሞች ፎረም ስኬታማ እንዲሆን ላበረከቱ አዘጋጆች፣ አጋር አካላት እና ተሳታፊዎች በሙሉ ምስጋና ያቀቡ ሲሆን፣ ከተሞቻችንን የብልጽግና ማዕከላትና ተምሳሌት የማድረግ ርዕያችንን ለማሳካት በጋራ አንነሳ በማለት በመዝጊያ መርሃ-ግብሩ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡