ህዳር 17, 2025

ህዳር 7 ቀን 2018 ዓ.ም (ከመልሚ)
ከተሞች ምቹ እና ለኑሮ ተስማሚ እንዲሆኑ በመሠራቱ በከተሞች የልማት ስራ ከፍተኛ መነቃቃት መፈጠሩን የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስትር ወ/ሮ ጫልቱ ሳኒ ገለፁ።

ሚኒስትሯ ይህን የተናገሩት ‘የከተሞች ዕድገት ለኢትዮጵያ ልህቀት’ በሚል መሪ ሀሳብ በአፋር ክልል ሠመራ-ሎጊያ ከተማ እየተካሄደ ያለውን 10ኛው የኢትዮጵያ ከተሞች ፎረም ሁለተኛ ቀን ውሎ አስመልክቶ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ነው።

ክብርት ሚኒስትር እንዳሉት ፎረሙ እንደሀገር በከፍተኛ ማንሰራራት ዘመን ላይ ባለንበት ወቅት መከበሩ ለየት ያለ ትርጉም አለው።

መንግሥት ከተሞችን አረንጓዴ እና ለኑሮ ምቹ ለማድረግ በልዩ ትኩረት እየሰራ መሆኑን ያነሱ ሲሆን፣ ይህ ጥረት በከተሞች ከፍተኛ መነቃቃትን ፈጥሮአል ብለዋል።

የዘርፉን ተወዳዳሪነት የሚያጎለብቱ እና ተግዳሮቶችን የሚያቃልሉ ገንቢ የፓናል ውይይቶችም እየተካሄዱ መሆኑን ጠቁመዋል።

ሚኒስትሯ በመግለጫቸው፣ ከዚህ ቀደም የድህነት ማሳያ የነበሩ ከተሞች በመንግሥት በተሰጠው ልዩ ትኩረት የብልጽግና ማሳያ እየሆኑ መምጣታቸውን ተናግረዋል።

በተለይም በአዲስ አበባ በከፍተኛ ፍጥነት እና ጥራት የተከናወነው የኮሪደር ልማት ለዘርፉ በርካታ ትሩፋቶችን ማስገኘቱን ጠቁመዋል።

የኮሪደር ልማት የኢንዱስትሪዎች መነቃቃትን፣ አዳዲስ የሥራ ዕድል መፍጠርን ማስቻሉን እንዲሁም የሥራ ባህልን በጉልህ የቀየረ መሆኑን ተናግረዋል። ይህ ልማት የከተሞችን እንቅስቃሴ እና ገቢ በማሳደግ የአገልግሎት አሰጣጥ እንዲዘምን ማድረጉንም አብራርተዋል።

Posted in: ዜና