ህዳር 17, 2025

ህዳር 6/2018 ዓም(ሠመራ):-

የኢፌዴሪ ከተማና መሠረተልማት ሚኒስቴር ያዘጋጀው 10ኛው የከተሞችፎረም በአፋር ብሄራዊ ክልል ሠመራ-ሎጊያ ከተማ አስተናጋጅነት በደማቅ ስነሥርአት ቀጥሏል።

በፎረሙ የሕዳር 7/2018ዓ.ም የረፋድ ቆይታ ላይ ሁለተኛው የፓናል ውይይት መርሃግብር  ተካሂዷል።

በሡልጣን አሊሚራህ መታሠቢያ አዳራሽ በተካሄደው መርሃግብር  ላይ የሠመራ-ሎጊያ ከተማ ከየት ወዴት በሚል ርዕሰ  ጽሁፍ  ቀርቧል።

የአፋር  ቋንቋ ፣ባህልና ታሪክ  ጥናትና ምርምር  ኢንስቲትዩቱ  ዋና ዳይሬክተር  ዶ/ር  ሀቢብ አህመድ በቀረበው ጽሁፍ የአፋርና የኢትዮጵያ  የረጅም ዘመን በዋናነትም እስከ ቀይባህር  የዘለቀ የከተሜነት ታሪክ ተዳስሷል ።

አፋር የሰው  ዘር መገኛነቱ እና የመደማመጥ እሴት ባለቤትነቱም ተወስቷል።

አፋር ከጥንት የኢትዮጵያ  ታሪክ አንስቶ የክትመት ታሪክ ያለው ሲሆን፣ ይህም ከዳህላክ  ደሴቶች እስከ ደቡብ  ዘይላ ድረስ በተዘረጋው የቀይባህር  ጠረፎች ድረስ እንደሚካተትም ጽሁፍ አቅራቢው አመላክተዋል።

በመሆኑም የኢትዮጵያ  የወደብ ባለቤትነት ከቀይባህር  ተፈጥሯዊ ፣ ታሪካዊ እና ህጋዊ ባለቤትነት ብሎም ከአፋር  ህዝብ  ታሪክ ጋር የተቆራኘ ስለመሆኑም አብራርተዋል።

በማስከተልም የአፋር ታሪካዊ የየብስ ላይ ክትመት አሳይኢታ፣በማሥከተልም ሎጊያ፣ ከቅርብ አመታት ወዲህ ደግሞ ሠመራ-ሎጊያ ስለመሆናቸው አስረድተዋል።

በአሁኑ ወቅት የሠመራ-ሎጊያ ከተማ ሠፋፊ የመሠረተ ልማት ዝርጋታዎች  እየተከናወኑባት እንደሚገኙና በተለይም ባለፉት ሁለት አመታት የመንገድ፣የቤቶች፣የኮሪደር ልማት፣ የሞሰብ አገልግሎትን ጨምሮ ከፍተኛ ልማት እየተከናወነ ስለመሆኑ ዶ/ር ሀቢብ አህመድ ገልጸዋል።

የቀረበውን ጽሁፍ ተከትሎ በፓናሊስቶች እንዲሁም በተሳታፊዎች ውይይት  ተካሂዷል ።

በ10ኛው የኢትዮጵያ  ከተሞች ፎረም ከ150 በላይ ከተሞች እየተሳተፉ ነው።

Posted in: ዜና