ህዳር 18, 2025
ሠመራ፣ ህዳር 8 /2018 ዓ.ም ፣ (ከመልሚ)
የኢፌዴሪ ከተማና መሠረተ-ልማት ሚኒስቴር ያዘጋጀው 10ኛው የኢትዮጵያ ከተሞች ፎረም በአፋር ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት በሠመራ-ሎጊያ ከተማ አስተናጋጅነት በደማቅ ስነ-ሥርዓት በመካሄድ ላይ ነው።
በዛሬው ዕለት የሦስተኛ ቀን ውሎው በተለያዩ ርዕሰ-ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ ጥንታዊ ጽሁፎች በሱልጣን አሊሚራህ መታሰቢያ የስብስባ አዳራሽ ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል።
የቀረቡት ጥንታዊ ጽሁፎች ያተኮሩባቸው ርዕሰ -ጉዳዮችም በኢትዮጵያ ልማታዊ ሴፍቲኔትና የስራ ዕድል ፈጠራ ፕሮግራም ትግበራ የተገኙ ስኬቶችን በተመለከተ በአቶ ብርሃኑ ተሾመ፣ የሚኒስቴር መ/ቤቱ የፕሮጀክቱ ጽ/ቤት ሀላፊ የኢትዮጵያ መዋቅራዊ ፕላን አተገባበር በኦሮሚያ ክልል፣ በዶ/ር ደጉ በቀለ፣ ከሲቪል ሰርቪስ ዩኒሽርሲቲ ፤ በኢትዮጵያ የኢ-መደበኛ አሰፋፈር ተግዳሮቶችና የፖሊሲ መፍትሄዎች፣ በዶ/ር ውባለም ስራው ከኢትዮጵያ የፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት ቀርቧል።
የቀረበውን ጽሁፍ ተከትሎ በፓናሊስቶች በክቡር አምባሳደር ሽፈራው ተ/ማርያም(ዶ/ር) ፣ እንዲሁም ከሚኒስቴር መ/ቤቱ የመረትና ካዳስተር መሪ ስራ አስፈፃሚ በአቶ ብዙዓለም እድማሱ እና የከተማ ፕላን መሪ ስራ አስፈፃሚ በወ/ሮ ገነት ገ/እግዚአብሄር አወያይነት በተሳታፊዎች በርካታ ጥያቄና አስተያየቶች ቀርበው ውይይት ተካሂዶባቸዋል ።
በውይይቱ ማጠቃለያ ላይ ከመድረክ በተሰጠ አስተያየት በቀረቡት ሠነዶች ላይ ለተጠቀሱ ችግሮች ዘላቂ መፍትሔ ሊሆን የሚችለው የከተማ አመራር ስርዓትን ማሻሻል፤ ህግን በአግባቡ ማስተግበር እና በቴክኖሎጂ መታገዝና እሱን አጠናክሮ ማስቀጠል አስፈላጊ መሆኑ ተገልጿል።
በተመሳሳይ በሌላ አዳራሽ ከቀረቡት ጥንታዊ ጽሁፎች መካከል በኢ/ር ሀምዛ መሀመድ ከሀሮማያ ዩኒቨርሲቲ የቀረበው ጥልቅ የሆኑ የማዕድንና የአፈር ምርምሮችን ለኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው ግብአቶችን በሀገር ውስጥ አምርቶ ጥቅም ላይ በማዋል ሀገራዊ የተቀናጀ መሠረተ-ልማትን እውን ማድረግና በከተሞች አካታችና ቀጣይነት ባለው መልኩ ከመሬት በላይና በታች የሚከናወኑ መሠረተ-ልማቶች ለሁሉም ዜጎች ተደራሽና ምቹ ሆነው መገንባት እንዳለባቸው የሚገልጸው ጥናታዊ ጽሁፍ በሚኒስቴር መ/ቤቱ የመሠረተ ልማት ገንብ ተቋማት ቅንጅትን ስራ አስፈጻሚ አቶ ቴድሮስ ተገኝ ፤ እንዲሁም በቅንጅት ባለመስራት ሊፈጠር ስለሚችል የሀብት ብክነትና ሀገራዊ ጉዳት የሶማሌ ላንድ የሀርጌሳ ከተማ ተጨባጭ ሁኔታ በዶ/ር አህመድ ጃማ የሶማሌ ላንድ አስተዳደር የመሬት ዳይሬክተር ቀርቦ የጋራ ውይይት ተደርጔል።