ህዳር 11, 2025
አዲስ አበባ፣ ህዳር 2/2018 ዓ.ም፣ (ከመልሚ)
በአፋር ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት፣ ሰመራ ሎጊያ ከተማ ከህዳር 6-10 ቀን 2018 ዓ.ም “የከተሞች ዕድገት ለኢትዮጵያ ልህቀት!” በሚል መሪ ቃል የሚካሄደውን 10ኛውን የከተሞች ፎረም ዝግጅት መጠናቀቅና ፎረሙ የሚካሄድበት ቀን መቃረቡን በተመለከተ በዛሬው ዕለት በከተማና መሠረተ-ልማት ሚኒስቴር ጋዜጣዊ መግለጫ ተሰጠ፡፡
ጋዜጣዊ መግለጫውን የሰጡት ክብርት ሚኒስትር ወ/ሮ ጫልቱ ሳኒ በመግለጫቸው ከተማና ከተሜነት የሁሉም ነገር መገለጫዎች እንደሆኑ በማስታወስ በዝቅተኛ ደረጃ ላይ ይገኝ የነበረው የክትመት ምጣኔ በአሁኑ ሰዓት እያደገ መጥቶ በየዓመቱ በ5 ነጥብ አራት በመቶ ዕድገት እያስመዘገበ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
እስካሁን በተካሄዱ ፎረሞች የተገኘው ለውጥና የከተሞች ዕድገት አሁን ላለንበት የዕድገት ምዕራፍ እንዳሸጋገረንና ይህ የለውጥ ዕርምጃ በ10ኛው የከተሞች ፎረም የበለጠ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልና ከተሞች እርስ በርስ የሚማማሩበት መድረክ እንደሚሆን ይጠበቃልም ብለዋል፡፡
በዘርፉ የታየውን ዕድገት በማስመልከትም በማሳያነት በክቡር ጠ/ሚ/ር ዐብይ አህመድ (ዶ/ር) ሀሳብ አፍላቂነት በአሁኑ ሰዓት ከ73 ከተሞች በላይ በኮሪደር ልማት እየተሳተፉ እንደሆነና ይህም ከተሞች የራሳቸውን የገቢ አቅም ለማሳደግና ለዜጎች የስራ ዕድል የሚፈጥሩበትን ምቹ ሁኔታ እየፈጠረላቸው እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
የ10ኛው የከተሞች ፎረም ላይ በፎረሙ ላይ የሚሳተፉ ከተሞችና የእህትማማች ከተሞች ምዝገባ የተጠናቀቀ ሲሆን በፎረሙ ላይ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትና የፋይናንስ ተቋማት ሁሉ የሚሳተፉበት ይሆናል፡፡
ይህም ከተሞች እርስ በርስ ተያይዘው የሚያድጉበትን፣ የፖሊሲ ግብአት የምናገኝበትን፣ ከተሞች ተጨማሪ አቅም የሚገነቡበትን፣ የዜጎችን ፍላጎት ያሟሉና ዓለም አቀፍ ስታንዳርዶችን ያሟሉ ከተሞችን በመገንባት ወደ አፍሪካና ወደ ዓለም ደረጃ ለማደግ የምናደርገውን ጉዞ ለማገዝ የሚያስችለንን አቅም የምንፈጥርበት ስለሆነ የከተሞች ፎረም መካሄድ ትልቅ አቅም ይሆነናል ብለዋል፡፡