ህዳር 17, 2025
ሁለተኛ ቀኑን በያዘው 10ኛው የኢትዬጵያ ከተሞች ፎረም የተለያዩ ጥናታዊ ጽሁፎች በሙህራን ቀርበው ውይይት እየተደረገባቸው ይገኛል።
ውይይት ከተደረገባቸው ጥናታዊ ጽሁፎች አንዱ አገር አቀፍ የመንግስት አገልግሎትና አስተዳደር ሪፎርም ጥናት ነው። ጥናታዊ ጽሁፉን ያቀረቡት የኢፌድሪ ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ክቡር ዶ/ር መኩሪያ ሀይሌ ናቸው። ኮሚሽነሩ የመንግስት ስራ አስፈጻሚ መዋቅር በአንድ ሀገር የፖለቲካ ድርጅት በተቀያየረ ቁጥር መቀያየር የሌለበት ዘመን ተሻጋሪ እና ፓርቲ ተሻጋሪ መሆን እንዳለበት ገልጸዋል።
በዚሁ መሰረት የመንግስት አገልግሎትና አስተዳደር ሪፎርም ሰባት መሰረታዊ አምዶች ያሉት መሆኑን ጠቅሰው አላማውም ሰራተኛውን መቀነስ ሳይሆን በመንግስት አገልግሎትና አስተዳደር ላይ ያለውን የአቅም ክፍተት በመለየት ሰራተኛውን ለተልዕኮ ለማዘጋጀት እና ዘላቂ ተቋማት ለመገንባት ነው ብለዋል።
በተያያዘም ብሔር ብሄረሰቦችን፣ ጾታን፣ እድሜን እና የአካል ጉዳትን ማዕከል ያደረገ ብዝሀነትና አካታችነትን ማስፈን ዘላቂ ሀገረ መንግስት ለመገንባት ወሳኝ መሆኑን ክቡር ኮሚሽነሩ አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።
የሪፎርሙ አንዱ አካል የሆነው ዘመናዊ የኢትዬጵያዊያን አገልግሎት ለተቀናጀ እድገት (Modern Ethiopian Service for Organized Benifits, MESOB) በተለያዩ ቦታዎች ተበታትነው የሚሰጡ አገልግሎቶችን ዘመናዊ፣ ቀልጣፋ፣ ጊዜና ወጪ ቆጣቢ በሆነ መልኩ ለማሰለጥ እንዲረዳ በማሰብ በክቡር የኢፌድሪ ጠቅላይ ሚኒስቴር ዶክተር አብይ አህመድ ሀሳብ አመንጭነት በፌደራልና በክልሎች ደረጃ እንደተጀመረ ተናግረዋል። በዚሁ መሰረት በቀጣይ በከንቲባ ደረጃ በሚመሩ ከተሞች አገልግሎቱ እንዲጀመር በመንግስት አቅጣጫ መቀመጡን አስገንዝበዋል።
በፎረሙ ላይ ከተለያዩ ከተሞች የተውጣጡ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች፣ ባለሙያዎች እና የዩኒቨርሲቲ ምሁራን እየተሳተፉ የሚገኙ ሲሆን የቀረበው ጥናት የከተሞችን የአገልግሎት አሰጣጥ ደረጃ ለማሰድግ እንደሚረዳና የተጀመረውም ስራ አበረታች መሆኑን ገልጸዋል። ፓናሉ በሌሎች የጥናት ጽሁፎችም ይቀጥላል።