ህዳር 17, 2025

በዛሬው እለት በ10ኛው የኢትዮጵያ ከተሞች ፎረም ላይ ለመከፋል የሰው ልጅ መገኛ በሆነው በአፋር ክልል በፈጣን የብልጽግና ጉዞ ላይ በሚትገኘው በሰመራ ከተማ ተገኝተናል።

በምሽቱም ዘመናዊነትን ከክልሉ ሕዝብ ባህል፣ ወግና እሴት ጋር በማዋሀድ በተፋጠነ መልኩ እየተገባደደ የሚገኘውን የሰመራ ከተማ የኮሪደር ልማት ስራ ጎብኝተናል።

ሰመራ ከተማ በፕላን የከተመች መሆኑ፣ ስትራቴጂያዊ አቀማመጧና ከወንድሜ ክቡር ርዕሰ መስተዳድር ሃጂ አወል አርባ ጀምሮ የክልሉና የከተማ አስተዳደሩ አመራርና ሕዝብ ትጋትና ቁርጠኝነት በሰጣት እድል በፈጣን እድገት ላይ ስትሆን የፓርቲያችን የኮሪደር ልማት እሳቤ ደግሞ ተጨማሪ ውበትና እሴት አላብሷታል።

በተለይም የኮሪደር ልማት ስራው ዘመናዊነትን ብቻ ሳይሆን የሕዝቡን ባህላዊ ትውፊቶች በማንፀባረቅ ለአብነትም የአፋር ህዝብ በመለያነት የሚታወቅባቸውን ጊሌ፣ ግመል፣ ባህላዊ ወፍጮ፣ ባህላዊ የወንዶች ትራስ፣ ሰሌን እና የወተት መጠጫ (ካኡንታ) በኮሪደር ልማቱ የተካተቱበት መንገድ እጅግ ያስደንቃል።

በመሰረታዊ ግንባታዎች ደረጃም 2 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለውና 6 ተሽከርካሪዎችን በምቾት ሊያስተናግድ የሚችል መንገድ፣ የእግረኛ መንገድ፣ የብስክሌት መንገድ እንዲሁም መንገድንና አረንጓዴ ልማትን ያማከሉ የተቀናጁ መሰረተ ልማቶች የተሟሉለት የኮሪደር ልማት ስራ ነው።

በቀጣይም እንደ ብልፅግና ፓርቲ መሰል ዘመናዊነትን ከሀገራችን ሕዝቦች ማንነት፣ ታሪክ፣ ባህል እና እሴት ከሚያንፀበርቁ መለያዎች ጋር የሚያዋህዱ የልማት ስራዎችን በስፋት የመስራት ጥረታችንን አጠናክረን እንደምንቀጥል በዚህ አጋጣሚ ለማረጋገጥ እወዳለሁ።

Posted in: ዜና