Web Content Display Web Content Display
Minimize Maximize

 

በበጀት ዓመቱ ከ35 ሺህ በላይ ቤቶች እንደሚገነቡና ለ25ሺህ ዜጎች የሥራ ዕድል እንደሚፈጠር የክልሉ ከተማ ልማትና ቤቶች ቢሮ አስታወቀ፡፡

የቤት ግንባታ ኘሮግራሙ በማህበራት፣ በመንግስት አስተባባሪነትና በሪል ስቴት አልማዎች የሚከናወን ይሆናል፡፡

ጉዳዩንም አሥመልክቶ በከተማ ልማትና ቤቶች ቢሮ የቤቶች ልማትና አስተዳደር ኤጀንሲ ከባለድርሻ አካላት ጋር የምክክር መድረክ በወላይታ አካሒዷል፡፡ 

ዝርዝሩ እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡

በክልሉ የከተሞችን ዕድገትና መሥፋፋት ተከትሎ የመኖሪያ ቤት ፍላጎት ቁልፍ የመልካም አስተዳደር ችግር እየሆነ መጥቷል፡፡

ችግሩንም ለመቅረፍ መንግስት የቤት ልማት ፖሊሲና ስትራቴጅ እንዲሁም ደንቦችና መመሪያዎችን በማጽደቅ ዘጠኝ የቤት ልማት አማራጮችን አቅርቧል፡፡

በከተማ ልማትና ቤቶች ቢሮ የቤቶች ልማትና አስተዳደር ኤጀንሲ ዳይሬክተር አቶ አስቻለው ካሳዬ ለመድረኩ ተሳታፊዎች እንደተናገሩት፣ በከተሞች ጉልቶ የሚታየውንና የመልካም አስተዳደር ቁልፍ ችግር የሆነውን የመኖሪያ ቤት ፍላጎትና አቅርቦት ለማጣጣም ክልሉን ዘጠኝ የቤት ልማት አማራጮች ማቅረቡንና ከነዚህም መካከል የማህበር ቤት ልማት ኘሮግራሙ በክልሉ በሰፊው ተግባራዊ  እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡

በዚህም በጀት ዓመቱ በከተማና በገጠር ከ35 በላይ የመኖሪያ ቤቶች ግንባታ በማካሔድ ለ23 ዜጎች የሥራ ዕድል በመፍጠር በቅድመ ምዝገባና ዕውቅና ሒደት ላይ 2 ቢሊየን ብር ለመቆጠብ ዕቅድ ተይዞ እየተሰራ እንደሚገኝ ዳይሬክተር ተናግረዋል፡፡

ከሚገነቡት ቤቶች መካከል 87 በመቶው በማህበር ቤት ኘሮግራም የሚከናወናውን ሲሆን 23753 በከተሞች፣ 7500 በገጠርና ቀሪዎቹ በመንግስት አስተባባሪነትና በሪል ስቴት አልሚዎች ተግባራዊ ይሆናል ብለዋል፡፡

በዚህም የመልካም አስተዳደር ችግሩ እንደሚቀረፍና ዝቅተኛና መካከልኛ ገቢ ያላቸው ዜጎች ተጠቃሚ እንደሚሆኑ አብራርተዋል፡፡

በምክክር መድረኩም በማህበር ቤት ልማት ኘሮግራሙ አፈፃፀም ፣ አጠቃላይ በ2008 በጀት ዓመት የተግባር ምዕራፍ መሸጋገሪያና በመንግስት ቤቶች መረጃ አያያዝ ሰነድ ላይ በሰፊው ውይይት ተደርጎበታል፡፡

ከዚህ ጋር ተያይዞ በጸደቀው የቤት አቅርቦት ፖሊሲና ስትራቴጅ ተግባራዊ ለማድረግ በሚደረገው ጥረት የተቀናጀ የመሰረተ ልማት አቅርቦት ማነስ፣ የለማ መሬት ዝግጅትና አቅርቦት ዝቅተኛ መሆን፣የከተማ ነዋሪዎች የገቢ መጠን ማነስና የግንባታ አቅርቦት እጥረትና የኮንስትራክሽን አቅም ደካማ መሆን በምክንያትነት ያጋጠሙ ችግሮች መሆናቸው ተጠቅሷል፡፡

የመድረኩ ተሳታፊዎች  በውይይቱ ላይ እንደተናገሩት፣በከተሞች የቤት ችግር ከስራ ዕድል ፈጠራ በባሰ ሁኔታ ቁልፍ ችግር እየሆነ መምጣቱን ጠቁመው፣በዚህ የሚፈጠረውን የመልካም አስተዳደር ችግር ለመቅረፍ አስፈላጊውን ዝግጅት ማድረግና ያለ ዕረፍት በንቅናቄ መፈጸም እንደሚገባቸው ገልጸዋል፡፡

በቀጣይ የማህበር ቤት ልማት ፕሮግራሙን ስኬታማ ለማድረግ የተጀመረውን ጥረት አጠናክሮ ለማስቀጠል መሬት በስፋት የሚቀርብበትን ሁኔታ ማመቻቸትና የግንዛቤ ማስቸበጫ እንቅስቃሴው ከመቸውም ጊዜ በላይ ትኩረት ተሰጥቶት ሊሰራበት እንደሚገባ ተሳታፊዎች አክለው ተናግረዋል፡፡