ዜና ኮሚኒኬሽን
ፐብሊክ ሰርቪሱ በተሰማራበት የስራ መስክ ተልዕኮውን ለመወጣት በተሟላ መልኩ ርብርብ ማድረግ ይጠበቅበታል አለ የክልሉ ከተማ ልማትና ቤቶች ቢሮ፡፡
ቢሮው ይህንን ያለው የሲቪል ሰርቪስ ቀንን ምክንያት በማድረግ " በስነ ምግባሩ የተመሰገነ ፐብሊክ ሰርቪስ ለኢትዮጵያ ህዳሴ" በሚል መሪ ቃል በዓሉን በቢሮ ደረጃ ባከበረበት ወቅት ነው፡፡
ብቁና ውጤታማ ፐብሊክ ሰርቪስ መገንባት ለክልላችን ብሎም ለሃገራችን ህዳሴ ያለውን ፋይዳ፣ የለውጥ ጉዞ አወንታዊ ሚና፣ ጉድለቶችና የቀጣይ አቅጣጫዎች ላይ ትኩረት በማድረግ በፕሮግራሙ ላይ ሰፊ ውይይት ተደርጓል፡፡
በዚህም ፐብሊክ ሰርቫንቱ ለልማታዊና ለዲሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ የሚያበረክተው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ቢሆንም ያልተሻገሯቸው ጉዳዮች መኖራቸው ተጠቅሷል፡፡
የክልሉ ከተማ ልማትና ቤቶች ቢሮ ሃላፊ አቶ ክፍሌ ገ/ማርያም በፕሮግራሙ ላይ ተገኝተው እንደተናገሩት፣ ሲቪል ሰርቪሱ ብቁ፣ ተወዳዳሪና ውጤታማ በመሆን ለተሰጧቸው ተልዕኮዎች ስኬት ርብርብ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል ነው ያሉት፡፡
በጥልቅ ተሃድሶው ነጥረው የወጡ የልማትና የመልካም አስተዳደር ችግሮች፣ ኪራይ ሰብሳቢነትና ብልሹ አሰራሮች በከተሞች ደረጃ ለመፍታት ጠንካራ ትግል እየተደረገ ቢሆንም ባልተሸገርናቸው ችግሮች ላይ ሰፊ ርብርብ ማድረግ ይኖርብናል ብለዋል፡፡
በተለይም የአገልግሎት አሰጣጥ ቀልጣፋ ያለመሆንና ከዚህ ጋር ተያይዞ በሚነሱ የመልካም አስተዳደር ማነቆዎች ላይ በዋናነት ትኩረት ተሰጥቶ ሊሰራበት እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡
ከዚህ ጋር ተያይዞ የሚፈጠረው ችግር ዋና መንስኤ ለስልጣንና ለህዝብ አገልግሎት ያለው አመለካከት የተዛባ መሆን ሲሉ ቢሮ ሃላፊው ገልጸዋል፡፡
ፕሮግራሙን አስመልክቶ የመወያያ ሰነድ የቀረበ ሲሆን፣ ሰነዱም የፐብሊክ ሰርቪሱ በጥልቅ የመታደስ አስፈላጊነትና አስራ ሁለቱን የስነ ምግባር መርሆች ያካተተ ነው፡፡
በቀረበው ሰነድ ላይም ሰፊ ውይይትና የጋራ መግባባት ላይ ተደርሷል፡፡
የስነ ምግባር መርሆቹ የችግሮች መፍቻ ቁልፍ ናቸው ያሉት የመድረኩ ተሳታፊዎች፣ ውጤታማ ስራዎችን ለማስመዝገብ ሲቪል ሰርቫንቱ ከመርሆቹ አኳያ ተግባራትን መፈጸም ይኖርበታል ብለዋል፡፡
ከጥልቅ ተሃድሶው በኋላም በአንዳንድ አካባቢዎች የአገልጋይነት ስሜትን ተላብሶ ከመስራት፣ የውሸት ሪፖርትን ከመቀበልና ከመስጠት፣ የመንግስትን የስራ ሰዓት በሚገባ ከመጠቀም፣ በግዥ አካባቢ በጊዜና በጥራት ከመፈጸም አኳያ የሚስተዋሉ ችገሮች መኖራቸው በዋናነት ተጠቅሷል፡፡
በመሆኑም በቀጣይ የስነ ምግባር መርሆቹን በአደረጃጀቶች ላይ በመደበኛነት ውይይትና የዕቅድ አካል በማድረግ ለተግባራቱ ስኬት ሁሉ አቀፍ ርብርብ ማድረግ ይጠበቅብናል ብለዋል፡፡
በመጨረሻም ባለ ሰባት ነጥብ የአቋም መግለጫ በማውጣትና ቃል በመግባት የሲቪል ሰርቪስ ቀኑን በደማቅ ሁኔታ አክብረው ውለዋል፡፡
ዘገባውን ያደረሰው የክልሉ ከተማ ልማትና ቤቶች ቢሮ መንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ነው፡፡
ዜና ኮሚዩኒኬሽን
በደቡብ ክልል አዲሱን የስራ ላይ ምዘና የሙከራ ትግበራ እንዲያከናውኑ ከተደረጉ 44 ተቋማት መካከል 37ቱ ተቋማት ሙሉ በሙሉ ማጠናቀቃቸው ተገለጸ፡፡
ይህ የተገለጸው የክልሉ ከተማ ልማትና ቤቶች ቢሮ ከክልሉ ፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሃብት ቢሮ ጋር በመተባበር ለዞን መምሪያና ለልዩ ወረዳ ጽ/ቤት ሃላፊዎች እንዲሁም ለ28 ከተማ አስተዳደር ስራ አስኪያጆችና ለሰው ሃብት ባለሙያዎች በአዲሱ የስራ ላይ ምዘና ስልጠና በሰጠበት ወቅት ነው፡፡
መንግስት የበለጸገች ኢትዮጵያን ለመፍጠር የተለያዩ የልማትና መልካም አስተዳደር ፖሊሲዎችንና ስትራቴጅዎችን ቀርጾ ተግባራዊ እያደረገ ይገኛል፡፡
እነዚህን ፖሊሲዎችና ስትራቴጅዎች የማስፈጸም ኃላፊነት የተሰጣቸው ልዩ ልዩ የመንግስት ተቋማትም የሚጠበቅባቸውን ውጤት ማሳካት ይችሉ ዘንድ በዕውቀቱ የበለጸገና በአመለካከቱ የህዝብ አገልጋይነት የተላበሰ የመንግስት ሰራተኛ መገንባት ያስፈልጋል፡፡
በመሆኑም መንግስት የሃገሪቱን ፐብሊክ ሰርቪስ ችግሮች በማጥናትና በዘርፉ ውስጥ የሚታዩ ተግዳሮቶችን በመለየት የሪፎርም ፕሮግራሞችን ነድፎ ተግባራዊ እንቅስቃሴ እያደረገ ይገኛል፡፡
ከእነዚህም የሪፎርም ፕሮግራሞች መካከል አንዱ የፐብሊክ ሰርቪስ ማሻሻያ ፕሮግራም ሲሆን፣ በፕሮግራሙ ከታቀፉት ፕሮጀክቶች መካከል የስራ ላይ ምዘናና የደረጃ አወሳሰን አንዱ ነው፡፡
የክልሉ ፐብሊክ ሰርቪስና ሰው ሃብት ቢሮ ም/ቢሮ ሃላፊና የሰው ሃብት ልማትና ስራ አመራር ዘርፍ ሃላፊ አቶ መኮንን ደስታ እንደተናገሩት፣ በክልሉ ፐብሊክ ሰርቪስና ሰው ሃብት ቢሮ የተጀመረው አዲሱ የስራ ላይ ምዘናና የደረጃ አወሳሰን የአሰራር ስርዓት በ2ኛው ዙር 23 ተቋማትና በ3ኛው ዙር በ20 ተቋማት ላይ የሙከራ ትግበራ ስራ እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ከዚህ ጋር ተያይዞ በሚያዚያ ወር መጨረሻ የክልሉ ፐብሊክ ሰርቪስና ሰው ሃብት ቢሮ ሙሉ በሙሉ ወደ ሙከራ ትግበራ የገባበትና በመቀጠልም 23 ተቋማት በተመሳሳይ ሁኔታ በተሟላ መንገድ ተግባራዊ ማድረጋቸውን ም/ቢሮ ኃላፊው ገልጸዋል፡፡
በሙከራ ትግበራው ወቅት ያጋጠሙት ችግሮች ተለይተውና ተገምግመው ወደስራ እንዲገቡ በመደረጉ የተሳካ ስራ ተሰርቷል ነው ያሉት፡፡
በክልሉ የሙከራ ትግበራውን እንዲያከናውኑ ከተደረጉት 44 ተቋማት መካከል 37ቱ ሙሉ በሙሉ ማጠናቀቃቸውን የተናገሩት አቶ መኮንን፣ በቀሪዎቹ ተቋማት የተመዘኑት ስራዎች ከታችኛው መዋቅር መዘርዝሮች ጋር ባለመጣጣሙ በፌደራል ደረጃ እንደገና እንዲታዩ መደረጉን ጠቁመዋል፡፡
ጥናቱ ተጠናቅቆ እንደመጣ የሙከራ ትግባራው በሁሉም ተቋማት ላይ ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ይደረጋል ብለዋል፡፡
በክልሉ ከተማ ልማትና ቤቶች ቢሮ የሰው ሀብት ስራ አመራር ደጋፊ የስራ ሂደት ባለቤት አቶ ራህመቶ ቦካ እንደገለፁት፣ የስራ ላይ ምዘናው ለዕኩል ተግባር እኩል ክፍያ እንዲፈፀም የሚያደርግ በመሆኑ የሠራተኛውን ፍሰት በመቀነስና ፍትሀዊ የደመወዝ ክፍያ ስርዓት እንዲፈጠር በማድረጉ ረገድ ፋይዳው የጎላ ነው ብለዋል፡፡
ቢሮው በሁለተኛው ዙር የሙከራ ትግባራ በመግባት 98 በመቶ የሚሆነውን ተግባር ማከናወኑን ጠቁመው፣ ሴክተሩ በስሩ በርካታ የስራ ዘርፎችን የያዘ በመሆኑ አንዳንድ ስራዎች ተመዝነው ባለመምጣታቸው ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ አለመሆኑን ተናግረዋል፡፡
በአሁኑ ወቅትም የሙከራ ትግባራውን ከዞን እስከታቸው መዋቅር ድረስ ለማውረድ የቅድመ ዝግጅት ስራ እየተሰራ ይገኛል ነው ያሉት፡፡
በስልጠና መድረኩ የተገኙ ተሳታፊዎችም የተለያዩ ጥያቄዎችንና አስተያየቶችን አንስተዋል፡፡
ከነዚህም መካከል የት/ት ዕድል አግኝተው የሄዱና በድልድል ወቅት ያልተገኙ ሰራተኞችን ከመመደብ፣ በአመራርነት የነበሩና የስራ አፈፃፀም የሌላቸውን ሰራተኞች ከማወዳደር፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የተጠኑና በደረጃ የተቀመጡ አንዳንድ መዋቅሮችን ከመመሪያው ጋር ከማጣጣም፣ ሚዛናዊነትን ሊያጓደሉ የሚችሉ መስፈርቶችን በተጨበጭ ከመለካት አንጻር በዋናነት ሊታዩ የሚገቡ ጉዳዮች መሆናቸው ተገልጿል፡፡
በተነሱት ጥያቄዎችና አሰተያየቶች ላይ ከመድረኩበቂ ምላሽ ተሰጥቷል፡፡
ዘገባውን ያደረሰው የክልሉ ከተማ ልማትና ቤቶች ቢሮ መንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ነው፡፡