የደቡብ ክልል የከተማ ልማትና ቤቶች ቢሮ ፣ የንግድና የኢንዱስትሪ ልማት ቢሮና የኢንቨስትመንት ኮሚሽን የጋራ ጉባኤ አካሔዱ፡፡ ጉባኤው በሴክተሩ የመጀመሪያ ዙር የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ አፈፃፀም በመገምገምና በቀጣይ የ5 ዓመት የዕቅድ ዘመን የጋራ መግባባት ላይ በመድረስ ብቁ ዕቅድና ፈፃሚ እንዲዘጋጅ ያስችላል ተብሏል፡፡
አቶ መለሰ ዓለሙ
ም/ርዕሰ መስተዳደርና የከተማ ልማትና ቤቶች ቢሮ ኃላፊ
የክልሉ ም/ርዕሰ መስተዳደርና የከተማ ልማትና ቤቶች ቢሮ ኃላፊ አቶ መለሰ ዓለሙ በጉባኤው ተገኝተው እንደተናገሩት፣ በጋራ የተካሄደው ጉባኤ የመጀመሪያ ዙር የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ በጋራ የታቀደና የተፈፀመ በመሆኑ በአፈፃፀሙ የተገኙ ጥንካሬዎችና ጉድለቶች በመለየት ትምህርት ለመውሠድና ለቀጣይ ተልዕኮ ሁሉ አቀፍ ዝግጅት እንዲደረግ ያስችላል ነው ያሉት፡፡በየጊዜው የሚመዘገቡ ውጤቶችን አጠናክሮ ለማስቀጠልና በመልካም አስተዳደርና በኪራይ ሰብሳቢነት የሚታዩ ችግሮች ለመቅረፍ አመራሩ ከመቼውም ጊዜ በላይ ትግል ማድረግ እንደሚገባው አሳስበዋል፡፡ም/ርዕስ መስተዳደሩ አክለውም ፣ የቀጣዩን የ5 ዓመታትና የ2008 በጀት ዓመት ዕቅድ ላይ ግልፅነት በመፍጠር መዋቅራዊ ለውጥ ማምጣት እንደሚገባና ሕዝቡም የልማቱ ተጠቃሚ እንዲሆን ለማስቻል ሰፊ ስራ መስራት ይጠበቅብናል ብለዋል፡፡
የጉባኤው ተሳታፊዎች በከፊል
የጉባኤው ተሣታፊዎች እንደገለጹት፣ በተለያዩ ዘርፎች ለተከናወኑት ዝቅተኛ አፈፃፀሞችና የመልካም አስተዳደር ችግሮች የአመራሩ ቁርጠኛ አቋም ያለመኖር እንደሆነ ገልፀው፣ በ2ተኛው ዙር የታቀዱ ዕቅዶችን ከግብ በማድረስ ሁለንተናዊ ንቅናቄ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው ተናግረዋል፡፡
በጉባኤው የሴ/ሩ የሕ/ተሰብ ተሣትፎና የመልካም አስተዳደር ዕቅድ ቀርቦ ውይይት የተደረገበት ሲሆን በኢንተርኘራይዞች ልማትና የሕ/ተሰብ ተሣትፎ ምርጥ ተሞክሮዎችና የተሻለ አፈፃፀም ያላቸው የክልል ተቋማት ፣ ዞኖች፣ ከተሞችና ልዩ ወረዳዎች በማቅረብ ሌሎች እንዲማሩበት ተደርጓል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ የ2007 በጀት ዓመት የለውጥና የልማት ሥራዎች አፈፃፀም ምዘና ውጤት በጋራ ቀርቦ የተሻለ አፈጻጸም ያስመዘገቡ ተቋማት ዕውቅናና ሽልማት ተሠጥቷቸዋል፡፡
የሸልማት አሰጣጥ ስነ ስርዓት በከፊል
በመጨረሻም የቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎችን በማስቀመጥ የከተማ ልማትና ቤቶች ቢሮ ከዞኖች ጋር የ2008 በጀት ዓመት ዕቅድ የግብ ስምምነት በመፈራረም ጉባኤ ተጠናቅቋል፡፡