መሬት በኢኮኖሚ ውስጥ ገብቶ የበኩሉን ሚና እንዲጫወትና ከመሬት ጋር ተያይዞ የሚፈጠረውን የኪራይ ሰብሳቢነትና የመልካም አስተዳደር ችግር ለመቅረፍ የመሬት መረጃ የአሠራር ስርዓት በዘመናዊ ቴኖሎጂ ሊታገዝ ይገባል፡፡ ሲሉ የደቡብ ክልል ም/ርዕሰ መስተዳደር አቶ መለሠ ዓለሙ አሣሠቡ፡፡
የመሬት መረጃ የአሠራር ስርዓት በክልሉ ለመጀመሪያ ጊዜ በአምስት ትልልቅ ከተሞች ትኩረት ተሠጥቶት እየተሠራ እንደሚገኝ ተገልጿል፡፡
ዝርዝሩ እንደሚከተለው
የከተማ መሬት መረጃ በአግባቡ ባለመመዝገቡና ባለመደራጀቱ የአገልግሎት አሠጣጡ እንዳይሣለጥ፣ የባለይዞታዎች ቦታና ንብረት ዋስትና እንዳይረጋገጥ፣ ለሕገ-ወጥ የመሬት ወረራ መበራከትና ከመሬት ጋር ተያይዞ ለሚሰጡ አስተዳደራዊና ሕጋዊ ውሣኔዎች ጥራት መጓደል ከፍተኛ ተጽዕኖ እያሳደረ መምጣቱ ተገለጸ፡፡
የደቡብ ክልል ም/ርዕሰ መስተዳደርና የከተማ ልማትና ቤቶች ቢሮ ኃላፊ አቶ መለሠ ዓለሙ እንደተናገሩት፣ መሬት በከተሞች የሚጠበቅበት፣ የሚለማበትና የሚተዳደርበት ፖሊሲ፣ የሕግ ማዕቀፎችና የአሠራር ሥርዓቶች ለኪራይ ሠብሣቢነት በር በማይከፍትና ለልማት በሚውል ደረጃ የመሬት መረጃ አያያዝ ስርዓት በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ባለመደገፉ ያለበት ደረጃ አሣሣቢ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በመሆኑም መሬት በኢኮኖሚ ውስጥ ገብቶ የበኩሉን ሚና እንዲጫወት ለማድረግና ከመሬት ጋር ተያይዞ የሚከሠቱ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት የአመለካከት ግንባታ ሥራው በአሠራር ሥርዓት እና በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ሊታገዝ ይገባል ሲሉ ም/ርዕሰ መስተዳድሩ አሣስበዋል፡፡
በከተሞች ውስጥ ከሚንቀሣቀሠው ካፒታል ትልቁን ድርሻ የሚይዘው መሬት አንደሆነ የተናገሩት አቶ መለሠ፣ ለምርታማነትና ለአገልግሎት በማዋል የማምረቻ ኢንዱስትሪ ስራዎችን በከተሞች አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚቻል ገልፀዋል፡፡
በዘርፉ የተቀመጡ ግቦችን ለማሣካትና የሚፈለገውን ውጤት ለማስመዝገብ አመራሩ፣ ባለሙያውና ሕዝቡ ንቁ ተሣትፎ በማድረግ የሥራው ባለቤት ሊሆን ይገባል ሲሉም ም/ርዕሰ መስተዳድሩ መልክት አስተላልፈዋል፡፡
በከተማ ልማትና ቤቶች ቢሮ የከተማ መሬት ይዞታ ምዝገባና መረጃ ኤጀንሲ ዳይሬክተር አቶ አያኖ ሱመኖ በበኩላቸው፣ የመሬት ይዞታ ምዝገባና መረጃ ስርዓት ጊዜ የማይሠጠው ጉዳይ እንደሆነ አመላክተው፣ የመሬት መረጃ አያያዝ ስርዓቱን በማዘመን ከተሞች ያላቸውን የመሬት መጠን ለይተው እንዲያውቁና ለሌሎች የልማት ሥራዎች ምቹ ሁኔታን እንዲፈጥሩ ያስችላቸዋል ብለዋል፡፡
አቶ አያናው በመቀጠልም በክልሉ ለመጀመሪያ ጊዜ በአምስት ትልልቅ ከተሞች የመሬት ይዞታ ማረጋገጥና ምዝገባ የቅድመ ዝግጅት ሥራው እየተሠራ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡
በከተሞች የመሬት ይዞታ ማረጋገጥና ምዝገባ ለመጀመር በሚደረገው ጥረት የቅድመ ዝግጅት ሥራው ያለበት ደረጃም ተገምግሟል፡፡
ህገ ወጥ ግንባታን ስርዓት ከማስያዝ፣ድንበር ከማካለል፣ነባር የይዞታ መረጃዎችን ከማደራጀት፣ የሰው ሃይል ልማቱንና ቁሳቁሱን ከማሟላት አንጻር አበረታች ውጤቶች መመዝገባቸውንና በቀጣይ ለሚሰሩ ስራዎች ምቹ ሁኔታዎች እየተፈጠሩ እንደሚገኙ የመድረኩ ተሳታፊዎች ተናግረዋል፡፡