አዲስ አበባ፣ ህዳር 5/2017 ዓ.ም (ከመልሚ)
በአዲስ አበባ ከተማ ከግንቦት 11-15/2017 ዓ.ም የሚካሄደውን 20ኛው አህጉር አቀፍ ኮንፈረንስ የተመለከተ ጋዜጣዊ መግለጫ በከተማና መሠረተ-ልማት ሚኒስቴር፣ በኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር እና በዓለም ስራ ድርጅት በጋራ ተሰጠ፡፡
በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ የከተማና መሠረተ-ልማት ሚኒስቴር ሚኒስትር፣ ክብርት ወ/ሮ ጫልቱ ሳኒ፤ የከተማና መሠረተ-ልማት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ፣ ክቡር አቶ የትምጌታ አስራት እና የዓለም ስራ ድርጅት የአፍሪካ ቀንድ ተወካይ ሚስተር ካባ ዱምባላ የተገኙ ሲሆን የሚካሄደውን ሁነት የተመለከተ ጋዜጣዊ መግለጫ በጋራ ሰጥተዋል፡፡
እንደ ክብርት ሚኒስትር ወ/ሮ ጫልቱ ሳኒ ገለጻ ከመሠረተ-ልማት ዉጪ የሚመጣ የኢኮኖሚ ዕድገት እንደማይኖር ገልጸው ኮንፈረንሱ የሀገራችን ርዕሰ-መዲና፣ የዲፕሎማቲክ እና የአፍሪካ ህብረት መቀመጫ በሆነችው አዲስ አበባ መካሄዱ በርካታ ዕድሎችን ይዞ የሚመጣና ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ የመጣውን የሀገራችን አቅም ማሳያ ተደርጎ የሚወሰድ እንደሆነ በማስታወስ ሠፊ የስራ ዕድልን በሚፈጥሩ የመሠረተ-ልማትና የኮንስትራክሽን የሥራ መስኮች ላይ ትኩረቱን አድርጎ መካሄዱ ይበል የሚያሰኝ ተግባር እንደሆነና ሁነቱ ከኮንፈረንሱ ጎን ለጎን በኤግዚቪሽኖች፣ በፓናል ውይይቶች እና በመስክ ጉብኝቶች ታጅቦ የሚካሄድ በመሆኑ ሀገራችንን ለማስተዋወቅ የተሻለ ዕድል ይፈጥርልናል ብለዋል፡፡ በመጨረሻም ይሄ አህጉር አቀፍ ሁነት በስኬት እንዲጠናቀቅ ለኮንፈረንሱ ስኬታማነት ሁላችንም ርብርብ ልናደርግና ሀገራዊ ግዴታችንን በሚገባ ልንወጣ ይገባል ብለዋል፡፡
የዓለም ስራ ድርጅት የአፍሪካ ቀንድ ተወካይ ሚስተር ካባ ዱምባላ በገለጻቸው በተለያዩ ዙሮች በተለያዩ ሀገራት የተካሄዱ ኮንፈረንሶችን በዝርዝር በማስታወስ ኢትዮጵያ ለ17ኛ ጊዜ በተካሄደው ፎረም ላይ በነበራት ተሳትፎ እና አሁን ላይ በምትገኝበት ቁመና ለዚህ እድል እንደበቃች ገልጸው የዓለም ስራ ድርጅት ከአፍሪካ ዩኒየን ጋር በመተባበር ለኮንፈረንሱ ስኬታማነት ርብርብ እንደሚያደርግም ገልጸዋል፡፡
የከተማና መሠረተ-ልማት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ፣ ክቡር አቶ የትምጌታ አስራት ለሁነት ዝግጅቱ ከተለያዩ ተቋማትና የሙያ ማህበራት የተወከሉ የስቲሪንግ ኮሚቴ እና የቴክኒክ ኮሚቴ አባላትን ባወያዩበት ወቅት እንደተናገሩት ኢትዮጵያ ይህን ዕድል ስትወስድ ከየትኛውም ጊዜ በተሻለና በበለጠ ሁኔታ ሁነቱን እንደምታካሂድ እምነት ተወስዶ ስለሆነ የምናገኛቸውን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጥቅሞች ታሳቢ ባደረገ፣ መልካም ሀገራዊ ለውጦች ስላሉንና የመንግስት ዝግጁነትም በዛው ልክ ስለሆነ የተጣለብንን ትልቅ ሀገራዊ ኃላፊነት በብቃት በመወጣት የሀገራችንን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ለማረጋገጥ፣ የገበያ ዕድሎችን ለማስፋት፣ ያለንን መልካም ተሞክሮ ለማጋራትና ከሌሎች ልምድ ለመውሰድ፣ የዕውቀት ሽግግር ለማድረግ፣ ለወጣቶች አማራጭ የሥራ ዕድልን ለመፍጠር፣ ቱሪዝምን ለማነቃቃት እንዲሁም ከሀገራት ጋር ያለንንን መልካም ግንኙነት የበለጠ ለማሳደግ የሁሉንም ሴክተር ተቋማትና የሙያ ማህበራትን ጥምረት በማካተት በትብብር መንፈስ ሁነቱ በደማቅ ሁኔታ ተጀምሮ እንዲጠናቀቅ መስራት ስላለብን ሁላችንም የዝግጅት ኮሚቴ ዓባላት ኃላፊነታችንን በብቃትና በትጋት እንድንወጣ አደራ ማለት እፈልጋለሁ ብለዋል፡፡
ኮንፈረንሱ “የበለጠ የሰው ኃይል በሚጠቀሙ የኢንቨስትመንት አማራጮች ጠንካራ ማህበረሰብ እና ጤናማ አካባቢን እንፍጠር” (Resilient Communities and Healthy Environment: the Employment Intensive Investment Program approach) በሚል መሪ ቃል የሚካሄድ ሲሆን በዘላቂ የልማት ግቦች የተቀመጡ ግቦችን ለማሳካት ይረዳል ተብሎ ይታሰባል፡፡
በጉባኤው ላይ የልማት አጋሮች፣ የዓለም አቀፍ ተቋማት፣ የግሉ ዘርፍ ተወካዮች፣ ምሁራንና ተመራማሪዎች ይሳተፉበታል፡፡
ሪፖርተር፡- ስለሺ ዘገዬ
የካሜራ ባለሙያ፡- ፈዬ ደሜ