
July 14, 2025
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 30/2017 ዓ.ም (ከመልሚ)
በ2018 ዓ.ም በሀገር አቀፍ ደረጃ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪውን ቁልፍ ችግር በአጭር ጊዜ በመፍታት አዎንታዊ ለውጥ ለማምጣት የሚያስችል በከተማና መሠረተ-ልማት ሚኒስቴር የተቋቋመና የኢንዱስትሪውን ተዋናዮች ያሳተፈ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ትራንስፎርሜሽን ስትሪንግ ኮሚቴ በዛሬው ዕለት ስራውን በይፋ ጀመረ፡፡
እንደሚታወቀው የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ለሀገር ልማት የሚያበረክተው አስተዋጽኦ ጉልህ መሆኑ ቢታወቅም ኢንዱስትሪው በአሁኑ ሰዓት በበርካታና ውስብስብ በሆኑ ችግሮች የተተበተበ በመሆኑ እነዚህን ችግሮች በተለመደው አስተሳሰብ እና አካሄድ ሊመቅረፍ ስለማይቻል የአተያይ እና የአካሄድ ለውጥ ማምጣት አስፈልጓል።
ስለሆነም እነዚህን ችግሮች በዘላቂነት ለመቅረፍ በጋራ ሰርተን ኢንዱስትሪው እንዲያድግ፣ ለሀገራችን ልማት የበለጠ አስተዋጽኦ እንዲያበረክት፣ እንዲሁም የሀገራችን ማንሰራራት ሂደት ብቻ ሳይሆን ውጤትም ጭምር መሆኑን ማረጋገጥ ስለሚገባ እንደ አዲስ የተቋቋመው ስትሪንግ ኮሚቴ ከኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ካውንስል የሚሰጡ አቅጣጫዎችን በመውሰድ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ትራንስፎርሜሽን ሥራውን የማስተባበር እና የመምራት ሚና እንዲጫወት ሥራውን በከፍተኛ ሀገራዊ ስሜት፣ በባለቤትነት እንዲያከናውን ከበላይ አመራሩ አቅጣጫ ተቀምጧል፡፡
የተዋቀረውን ስቲሪንግ ኮሚቴ ወደስራ ለማስገባት የተጠራውን የመጀመሪያ ስብሰባ አስመልክተው ክብርት ሚኒስትር ወ/ሮ ጫልቱ ሳኒ እንደተናገሩት ስራውን በተቀናጀና ጥብቅ በሆነ የአመራር መርህ ማስኬድ የግድ መሆኑን ገልጸው በማንኛውም የስራ እንቅስቃሴ ውስጥ የእርሳቸው ክትትልና ድጋፍ እንደማይለያቸው በማስታወስ የስራውን ሂደት በቅርበት እንደሚከታተሉት ገልጸዋል፡፡
የስቲሪንግ ኮሚቴ ሰብሳቢ ሆነው የተሰየሙት ክቡር አቶ የትምጌታ አስራት፣ የሚኒስቴር መ/ቤቱ የመሠረተ-ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ሲሆኑ የኮሚቴው አባላትም ከሚኒስቴር መ/ቤቱ፣ ከተጠሪ ተቋማትና ከግሉ ዘርፍ የተውጣጡ የስራ ኃላፊዎች የተካተቱበት ነው፡፡
በስቲሪንግ ኮሚቴው ስርም ከተለያየ ዲሲፕሊን የተውጣጡ 6 ቡድኖች የሚገኙ ሲሆን ዓባላቱም ለዘርፉ ዕድገት ጉልህ አስተዋጽኦ የሚያበረክቱ መሆናቸው በስቲሪንግ ኮሚቴው የታመነባቸው ናቸው፡፡
ስቲሪንግ ኮሚቴው የሚመራባቸው አሳታፊ በሆነ መንገድ የተዘጋጁት የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ትራንስፎርሜሽን ሮድማፕ፤ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ተወዳዳሪነት ምዘና እና ዕውቅና ማዕቀፍ፤ እንዲሁም የኮንስትራክሽን ዘርፍ የአሠራር ማነቆን ለመገምገምና ለማሻሻል የሚረዱ Ease of Doing Business Framework in construction Sector ሰነዶች ናቸው፡፡
የስቲሪንግ ኮሚቴው ሰብሳቢ ክቡር አቶ የትምጌታ አስራት የስቲሪንግ ኮሚቴውን የማስጀመሪያ መርሃ-ግብር ሲከፍቱ እንደተናገሩት ኢንዱስትሪውን የመለወጥ ዕድል ለእኛ ተሰጥቷል፡፡ስለሆነም ኢንዱስትሪውን በተሟላ ሁኔታ መለወጥ ይኖርብናል፡፡
በ10 ዓመቱ መሪ ዕቅዳችን የሀገራችን 20 የኮንስትራክሽን ኩባንያዎች ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነታቸውን በማሳደግ ወደውጭ ሀገር ሄደው በዘርፉ እንዲሰማሩ ግብ ተቀምጧል፡፡
ስለሆነም 9 ዓባላት ያሉት ስቲሪንግ ኮሚቴ የተቋቋመው የተቀመጠውን ሀገራዊ አቅጣጫ በመከተል በፍጥነትና በጥራት ለውጥ የሚያመጣ ስራ በመስራት ተወዳዳሪ የሆነ ኢንዱስትሪ ለመፍጠር ስለሆነ እነሆ የምናደርገው ጉዞ በዛሬው ዕለት በይፋ ተጀምሯል ብለዋል፡፡
አያይዘውም እኛ የምንገነባው ሀገርን ስለሆነ ትልቁ ለውጥ ሊመጣ የሚችለው ደግሞ የተዘጋጁት ሠነዶች መሬት ላይ ወርደው ተግባራዊ ሲደረጉ በመሆኑ የሀገራችን የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ለሀገር ብልጽግና ወሳኝ መሆኑን በማመን የስቲሪንግ ኮሚቴው ዓባላት የጉዳዩን ሀገራዊ ፋይዳና አንገብጋቢነት ከግንዛቤ ውስጥ በማስገባት ለሀገራችን የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ትንሳኤ የየበኩላቸውን አስተዋጽኦ ማበርከት እንደሚጠበቅባቸውና ኢንዱስትሪው ላይ ያለውን ትርክት ለመቀየር በቁርጠኝነት መስራት እንደሚጠበቅባቸው ገልጸው የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ትራንስፎርሜሽን ኢኒሼቲቭ ማስጀመሪያ ሀገራዊ ፕሮግራም (Construction Industry Transformation Initiative Launching Program) በቅርቡ እንደሚካሄድ በስብሰባው ማጠቃለያ ላይ ገልጸዋል።
ሪፖርተር፡- ስለሺ ዘገዬ
የካሜራ ባለሙያ፡- አስመላሽ ተፈራ