
May 15, 2025
አዳማ፣ ግንቦት 05/2017 ዓ.ም፣ (ከመልሚ)
በከተማና መሠረተ-ልማት ሚኒስቴር የመሬትና ካዳስተር መሪ ሥራ አስፈጻሚ በተያዘው በጀት ዓመት በመሬትና ካዳስተር ስራዎች ላይ የተሻለ አፈጻጸም ያላቸውን ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች በመምረጥ ለሌሎች ክልሎች፣ ከተማ አስተዳደሮችና ለተመረጡ ከተሞች እንደ ሀገር ወጥና ተናባቢ የአሠራር ስርዓትን ለመዘርጋት የሚያስችል የልምድና የተሞክሮ ልውውጥ መድረክ በዛሬው ዕለት አካሄደ፡፡
መድረኩን በክብር እንግድነት ተገኝተው የከፈቱት የከተማና መሠረተ-ልማት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ፣ ክቡር አቶ ፈንታ ደጄን በመክፈቻ ንግግራቸው እንዳሉት የከተማ መሬት ያለውን ፋይዳ እና ጠቀሜታ በመገንዘብ የከተማ መሬትን ቆጥሮና. መዝግቦ በመያዝ በተገቢው መንገድ ማስተዳደር እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡
እንደ ክቡር ሚኒስትር ዴኤታው ገለጻ በሀገራችን ከሚገኙ 6 ነጥብ 6 ሚሊዮን ፓርስሎች (ቁራሽ መሬቶች) ውስጥ ባዘጋጀናቸው የህግ ማዕቀፎችና የማስፈጸሚያ ሠነዶች እንዲሁም በየጊዜው ባደረግናቸው የጋራ ውይይቶች ከ3 ዓመት በፊት ከነበረበት የ10 በመቶ የምዝገባ ሂደት አሁን ላይ ወደ 27 በመቶ ማድረስ የተቻለ ስለሆነ መንግስት ለከተሞች በሰጠው ልዩ ትኩረትና በኮሪደር ልማቱ በተሰሩ ስራዎች የተገኙ ውጤቶችን እንደ ዕድል በመጠቀምና በማስቀጠል ከተሞች የኢንቨስትመንት መዳረሻ እንዲሆኑ መስራትና ለዘርፋችን ብሎም ለሀገራችን ዕድገት በበለጠ መትጋት ይጠበቅብናል ብለዋል፡፡
የእርሳቸውን ንግግር ተከትሎ ከከተማ መሬትና ካዳስተር ጋር በተያያዘ የአዲስ አበባ ከተማ የመሬት ይዞታ ፋይል ማዘመንና አገልግሎት አሰጣጥ ተሞክሮ፤ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል፣ የስልጤ ዞን፣ የዓለም ገበያ ከተማ በህገ-ወጥ የመሬት ወረራ መከላከል ላይ የተሰሩ ስራዎች ተሞክሮ፤ የጅማ ከተማ የመሬት ይዞታ ማረጋገጥና ምዝገባ ስራዎች ተሞክሮ፤ የአዲስ አበባ ከተማ የልማት ተነሺዎችን መልሶ የማቋቋም ተሞክሮ ሠነዶች ቀርበው በመጨረሻ ትኩረት የሚሹ የመሬትና ካዳስተር ስራዎችን የተመለከተ ሰነድ በሚኒስቴር መ/ቤቱ የመሬት ማኔጅመንትና አስተዳደር ዴስክ ቀርቦ በቀረቡት ሠነዶች መነሻነት የጋራ ውይይት ተደርጓል፡፡
የውይይት መድረኩን የመሩት የመሬትና ካዳስተር መሪ አስፈጻሚው አቶ ብዙአለም አድማሱ ከቤቱ ለተነሱ ሃሳብ፣ ጥያቄና አስተያየቶች በሰጡት ምላሽና የማጠቃለያ አስተያየት ላይ እንደተናገሩት የካዳስተር ስራ ቁልፍ ስራ በመሆኑ የከተማ አመራሩና ፈጻሚው ከልምድና ተሞክሮው ያገኘውን ዕውቀት ተጠቅሞ በፍጥነት ወደስራ መግባት እንዳለበትና ህብረተሰቡ በንብረቱ ተጠቃሚ የሚሆንበትን አገልግሎት መስጠትና መንግስት ከመሬት ሀብቱ ማግኜት የሚገባውን ጥቅም እንዲያገኝ ማድረግ ይገባል ብለዋል፡፡
ሪፖርተር፡- ስለሺ ዘገዬ
የካሜራ ባለሙያ፡- አስመላሽ ተፈራ