
April 30, 2025
አዳማ፣ ሚያዝያ 17/2017 ዓ.ም፣ (ከመልሚ)
የከተማና መሠረተ-ልማት ሚኒስቴር ከአማራ ክልል ከተማና መሠረተ-ልማት ቢሮ ጋር በመተባበር ያዘጋጁት ትኩረቱን በአማራ ክልል የማዘጋጃ ቤታዊ ገቢና በክልሉ በተዘጋጀው የታሪፍ ማሻሻያ ደንብ ቁጥር 220/2017 እንዲሁም በፌዴራል መ/ቤቱ በተለዩ የማዘጋጃ ቤታዊ ገቢ አርዕስትና አመዘጋገብ ላይ ያደረገ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ከሚኒስቴር መ/ቤቱ እና ከክልሉ ለተውጣጡ የሚመለከታቸው አመራሮችና ባለሙያዎች በአዳማ ከተማ ተሰጠ፡፡
መድረኩን በይፋ ያስጀመሩት በሚኒስቴር መ/ቤቱ የከተማ አመራር ፋይናንስና አገልግሎት መሪ ስራ አስፈጻሚ የሆኑት አቶ ደሳለኝ ገመቹ በመክፈቻ ንግግራቸው እንዳሉት የከተሞችን መስፋፋትና ዕድገት ተከትሎ እያደገ የመጣውን የነዋሪውን የመሠረተ-ልማት ፍላጎት ለማሟላት ብዙ ሀብትን ይጠይቃል፡፡ ልማቱ የሚጠይቀውን ወጪ ለመሸፈን ደግሞ የከተሞችን የውስጥ አቅም ማሳደግ ስለሚያስፈልግ የገቢ ርዕሶችን ማስፋት፣ የክፍያ ታሪፎችን ማሻሻል እና የታክስ ስርዓቱን ማዘመን እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል፡፡
የእርሳቸውን የመክፈቻ ንግግር ተከትሎ የአማራ ክልላዊ መንግስት የከተሞች አገልግሎት ገቢ አሰባሰብና ታሪፍ ማሻሻያ ደንብ ቁጥር 220/2017ን በተመለከተ የውይይት መነሻ ሠነድ ከአማራ ክልል በአቶ አይናለም በለጠ የቀረበ ሲሆን የማዘጋጃቤታዊ ገቢ አርዕስትና አመዘጋገብ ሠነድ በሚኒስቴር መ/ቤቱ ባለሙያ፣ በአቶ ፈቃደ ተ/ማርያም ቀርቧል፡፡
እንደ አቶ አይናለም ገለጻ በክልሉ የሚገኙ 728 ከተሞች ቀጣይነት ላለው የከተሞች ዕድገት ሀብታቸውን የተሻለ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ላለው ተግባር እንዲያውሉት ማድረግ ተገቢ እንደሆነ ገልጸው ለከተማ ህዝብ ዕድገትና ደህንነት የሚያገለግሉ ሀብቶችን በጥናት የመለየት፤ የገቢ ሰብሳቢ ተቋማትን አደረጃጀት ማሻሻል እና ከፍተኛ ገቢን ሊያመነጩ የሚችሉ የገቢ ርዕሶችን በመለየት የታሪፍ ምጣኔን ከወቅቱ የገንዘብ የመግዛት አቅም ጋር በማገናዘብ ገቢን በአግባቡ መሰብሰብና ጥቅም ላይ ማዋል እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል፡፡
አቶ ፈቃደ በበኩላቸው በፌዴራል ደረጃ የተለዩትን የገቢ ርዕሶች ሲተነትኑ እንደተናገሩት ተቋማት ገቢ መሰብሰብ ያለባቸው በሚሰጡት አገልግሎት ላይ ብቻ ተመስርተው እንደሆነና ተደራራቢ የታክስ ክፍያን ለማስቀረት የሌላውን ገቢ ሰብሳቢ ተቋም ድርሻ መሻማት እንደማያስፈልግ ገልጸዋል፡፡
በቀረቡት የውይይት መነሻ ሠነዶች ላይ ተመስርቶ በተደረገው የጋራ ውይይት ከተሳታፊዎች በርካታ ጥያቄዎችና አስተያየቶች የቀረቡ ሲሆን ለቀረቡ ጥያቄና አስተያየቶች ከሠነድ አቅራቢዎችና ከመድረክ መሪዎች በቂ ምላሽና ማብራሪያ ከተሰጠ በኋላ ቀጣይ የስራ መመሪያዎች ተቀምጠዋል፡፡
ሪፖርተር፡- ስለሺ ዘገዬ