June 16, 2025

አዳማ፣ ሰኔ 5/2017 ዓ.ም (ከመልሚ)

ከከተማና መሠረተ-ልማት ሚኒስቴር፣ ከስራና ክህሎት ሚኒስቴር፣ ከፌዴራል ቴክኒክና ሙያ ስልጠና ኢንስቲትዩት፣ እንዲሁም ከሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች የተውጣጡ የዘርፉ አመራሮችና ባለሙያዎች የተሳተፉበት በኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ የህንጻ ግንባታ ዘርፍ የአነስተኛና መለስተኛ ባለሙያዎች የሙያ ብቃት ምዘና አፈጻጸምን በጋራ የሚገመግም መድረክ በዛሬው ዕለት በአዳማ ከተማ ተካሄደ፡፡

መድረኩ በዋናነት የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪውን ለማሻሻልና ተወዳዳሪ ለማድረግ እንዲሁም የአነስተኛና መካከለኛ የኮንስትራክሽን ባለሙያዎችን የሙያ ብቃት አቅም ለማሻሻል ታልሞ የተዘጋጀ ነው፤በመሆኑም መድረኩ የአነስተኛና መካከለኛ የኮንስትራክሽን ባለሙያዎች አቅም እንዲገነባና በምዘና ብቃታቸው ተረጋግጦ በኢንዱስትሪው እንዲሰማሩ ከማድረግ ባለፈ መሪ መዛኞችን ለማፍራት የሚያስችል ነው፡፡

ይህን መድረክ በይፋ ያስጀመሩት የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ልማት መሪ ስራ አስፈጻሚ ተወካይ አቶ ከተማ አማረ ሲሆኑ በመክፈቻ ንግግራቸው እንዳሉት የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው ለሀገሪቱ የኢኮኖሚ ዕድገትና ለስራ ዕድል ፈጠራ ያለው አበርክቶ ከፍተኛ እንደሆነና በአሁኑ ሰዓት የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው በከፍተኛ ሁኔታ እየተነቃቃ ቢሆንም በተለያዩ ደረጃዎች መፈታት የሚገባቸው ፈተናዎች እንዳሉበት ገልጸዋል፡፡

ከዚሁ ጋር በማያያዝ ከተግዳሮቶች አንዱ የሆነውን ተወዳዳና ብቃቱ የተረጋገጠ ፕሮፌሽናል ባለሙያዎችን ለመፍጠርና አቅማቸውን ለማሳደግ በዘርፉ የአነስተኛና መለስተኛ ባለሙያዎችን የሙያ ብቃት ማሻሻል አስፈላጊ በመሆኑ ይህን ችግር በዘላቂነት በጋራ ለመፍታት በየደረጃው የሚገኙ የመንግስትና የግል ተቋማት ቅንጅትና ትብብር አስፈላጊ መሆኑን ገልጸው አነስተኛና መለስተኛ ባለሙያዎች በዕውቀት፣ በክህሎትና በአመለካከት የተሻሉ ሆነው እንዲገኙና የዘርፉን ተወዳዳሪነት ለማሻሻል የህንጻ ግንባታ ዘርፍ የአነስተኛና መለስተኛ ባለሙያዎችን የሙያ ብቃት ምዘና አፈጻጸም በየጊዜው እየገመገሙ ክፍተቶችን መሙላት ስለሚያስፈልግ የግምገማ መድረኩ ሊዘጋጅ ችሏል ብለዋል፡፡

የመክፈቻ ንግግሩን ተከትሎ የአነስተኛና መለስተኛ የኮንስትራክሽን ባለሙያዎች ምዘና እና የሙያ ብቃት ማረጋገጫ አፈጻጸም የመስክ ዳሰሳ ሪፖርት፤ የአነስተኛና መለስተኛ ባለሙያዎችን የሙያ ብቃት ምዘና ማረጋገጫ ለመስጠት ተሻሽሎ የወጣው መመሪያ ቁጥር 001/2009 ዓ.ም ከቀረበ በኋላ የቀረበውን ሪፖርትና መመሪያ መነሻ በማድረግ የጋራ ውይይት ተደርጎ ቀጣይ የመፍትሄ አቅጣጫዎች እንዲቀመጡ ተደርጓል፡፡

ዘገባ፡- በስለሺ ዘገዬ
ፎቶግራፍ፡- በድንቅነሽ ኤርቃሎ

Posted in: News