
May 15, 2025
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 4 ቀን 2017 ዓ.ም (ከመልሚ) የከተማና መሠረተ-ልማት ሚኒስቴር አመራሮች በዘርፉ ባለፉት አራት ዓመታት ተኩል የተከናወኑ አበይቲ አፈጻጸሞችን በዝርዝር ገምግመዋል፡፡
ግምገማው የተካሄደው ከሴክተሩ የ10 ዓመት የልማት ዕቅድ አንጻር ከ2013 እስከ 2017 ዓ.ም የመጀመሪያውን ግማሽ ዓመት አፈጻጸም በተደረገ የአዝማሚያ ጥናት ነው፡:
የከተማና መሠረተ-ልማት ሚኒስቴር ሚኒስትር ክብርት ወ/ሮ ጫልቱ ሳኒ እንደተናገሩት ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ባለፉት አራት አመታት ተኩል መላው የተቋሙ አመራሮችና ባለሙያዎች ባደረጉት ከፍተኛ ርብርብ በከተሞች ከፍተኛ የሆነ ለውጥ እየተመዘገበ መምጣቱን ገልጸዋል፡፡
ክብርት ሚነስትሯ አክለውም ከዚህ በፊት የተከናወኑ የተሻሉ ውጤቶችን አጠናክሮ በማስቀጠልና እስክሁን በከፊል ያላከናወናቸውን ስራዎች በቀሪ ጊዚያት ከመላው የተቋሙ አመራሮችና ባለሙያዎች ጋር ትኩረት ሰጥተን በቅንጅት መስራት ይገባናል ብለዋል፡፡
አመራሩ ከብልሹ አሠራር ራሱን በማራቅ የታቀዱ ዕቀዶችን ከሂደት አንጻር ሳይሆን ውጤትን መሠረት ያደረገ ስልትን ቀይሶ በመሄድ አራአያነት ያለው ስራ በመስራት የሀገራችንን ከተሞች የብልጽግና ማሳያ ማድረግ ይጠበቅብናል ብለዋል ክብርት ሚኒስትሯ፡፡
የጥናት ሰነዱን ያቀረቡት በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ አማካሪ የሆኑት አቶ ሀብታሙ መውደድ የሀገራችን ከተሞች ከለውጡ በፊት ለኑሮ የማያመቹ፤ ዘመናዊ የመረጃ ቋት ያልነበራቸውና የአንድን ከተማ መስፈርት የማያሟሉ እንደነበሩ ጠቅሰው ከለውጡ ማግስት ጀምሮ በበርካታ የሀገራችን ከተሞች የሚስተዋለው ፈጣን ዕድገት የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ክትትል እና ድጋፍ ታክሎበት መሆኑን በጥናት መረጋገጡን ተናግረዋል፡፡
የጥናት ሰነዱ ከቀረበ በኋላ በርካታ አስተያየቶች በግብዓትነት ቀርበዋል፡፡ ዕቅዶቹ በአተገባበር ወቅት በተለይ ከ2012 ዓ.ም ወዲህ የኮቪድ 19፣ የሰላምና ጸጥታ ጉዳይ፣ ከተቋማዊ አደረጃጀት ጋር ተያይዘው የነበሩ እንቅፋቶች ላልተከናወኑ ስራዎች እንደምክንያት በጥናቱ መካተት እንደነበረባቸው አመራሮቹ ሀሳባቸውን ገልጸዋል፡፡
በመጨረሻም ለተነሱት ጥያቄዎችና አስተያየቶች በክብርት ሚኒስትሯና በየደረጃው ባሉ አመራሮች ማብራሪያ እና ቀጣይ አቅጣጫ ተሰጥቷል።
ሪፖርተር፡- ሞገስ ዓሊ
ፎቶ ባለሙያ ፤- ፈየ ደሜ