May 29, 2025

አዳማ፣ ግንቦት 19 ቀን ፣2017 ዓ/ም (ከመልሚ) የመሬትና ካዳስተር መሪ ስራ አስፈጻሚ፣ በከተሞች ገቢ ሪፎርም ፕሮጀክት ጽ/ቤት እና በባሀርዳር ዩኒቨርሰቲ ትብብር አዲስ የለማ የከተማ መሬት የሊዝ መረጃ ስርዓት ለሙከራ ይፋ ተደርጓል፡፡

መድረኩን በንግግር ያስጀመሩት የከተማና መሰረተ ልማት ሚ/ዴኤታ ክቡር አቶ ፈንታ ደጀን እንደተናገሩት የሀገራችን ከተሞች እጅግ በፈጣን ሁኔታ እያደጉና እየሠፉ ከመምጣታቸው ጋር ተያይዞ የህዝብ ቁጥርም በዚያው ልክ በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ መምጣቱን ጠቅሰው አዲስ የለማ የከተማ መሬት የሊዝ መረጃ ስርዓትን ተግባራዊ በማድረግ ውስን የሆነውን የመሬት ሀብትን ከዘልማዳዊ አሰራር በመውጣት ሀብትን በዘመናዊ አያያዝ ማስተዳደር ይገባል ብለዋል፡፡

አዲስ የተዘጋጀው ዌብ ቤዝድ ጂአይ ኤስን መሠረት ያደረገ የከተማ መሬት የሊዝ መረጃ ሥረዓት ከሙከራ እልፎ ወደ ሥራ ሲገባ ፋይዳው ዘርፈ-ብዙ ነው ያሉት ክቡር ሚኒስቴር ዴኤታው መሬትን ብልሹ አሠራር ምክንያት የህብረተሰቡን የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት፣ ገቢን በአግባቡ ለመሰብሰብ፣ መሬትን ለማስተላለፍ፣ ለማስተዳደር እና ህገወጥ የመሬት ወረራን ለመከላከል ሶፍትዌሩ በርካታ ጠቀሜታ እንደሚኖረው ክቡር አቶ ፈንታ አስገንዝበዋል፡፡

የለማውን ሲስተም በሁሉም የሀገሪቱ ከተሞች ተግባራዊ ለማድረግ አስፈላጊውን መሠረተ-ልማት መዘርጋት፣ ትጉና ታታሪ ሠራተኞችን በመዋቅር በማካተት ከዚያም አልፎ በቂ እውቀትና ክህሎት ያላቸውን ባለሙያዎች በማሰልጠን ስራውን ማቀላጠፍ እንደሚገባ ሚኒስትር ዴኤታው አሳስበዋል፡፡

ሲስተሙን ሁሉም ክልሎች በወጥነት ሊጠቀሙበት እንደሚገባ ያነሱት ሚ/ዲኤታው መሻሻል የሚገቡትን እያሻሻልን፣ አስፈላጊ ግብዓቶችን በጋራ እያሟላን፣ ዘመኑ የሚጠይቀውን የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ተግባራዊ ለማድረግ ክትትልና ድጋፋቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ አደራ ብለዋል፡፡

ጥናቱን ያቀረቡት የባህርዳር ዩኒቨርስቴ አቶ ጌትነት ማሞ እንደተናገሩት የናሙና ጥናቱ የተካሄደው በአዲስ አበባ ፣ ባህርዳር፣ መቀሌ፣ ኦዳማ፣ ድሬደዋ ፣ ሐዋሳ እና ዎላይታ የሶዶ ከተሞች መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
የናሙና ጥናቱ የሊዝ አተገባበርን፣ ክፍያዎችን፣ ገቢን አሟጦ ለመሰብሰብ፣ የመረጃ ልውውጥን ለማቀላጠፍ፣ ህግን የተከተለ ጨረታ ለመተግበር፣ ሁሉንም መረጃዎች ያካተተ ፣ በሁሉም ቋንቋዎች መጠቀም የሚያስችል ስለሆነ ጠቀሜታው ከፍተኛ ነው ብለዋል አቶ ጌትነት፡፡

በቀጣይ የኢንፎረሜሽን ቴክኖሎጅ እና የጂአይኤስ ባለሙያዎች ስልጠናውን ወስደው ወደተግባር እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

ሪፖርተር:ሞገስ ዓሊ
የካሜራ ባለሙያ ፡-አስመላሽ ተፈራ

Posted in: News