May 29, 2025

አዲስ አበባ፣ግንቦት 15 ቀን፣ 2017 ዓ.ም (ከመልሚ) የከተማና መሰረተ-ልማት ሚኒስቴር እና የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ከዓለም የስራ ድርጅት (ILO) ጋር በጋራ “የማይበገር ማህበረሰብ እና ጤናማ አካባቢ የሰው ኃይልን በብዛት የሚጠቀሙ የኢንቨስትመንት ፕሮግራም አካሄዶች” በሚል መሪ ቃል በአፍሪካ ህብረት የመሰብሰቢያ አዳራሽ ከግንቦት 11/2017 ዓ.ም ጀምሮ ለአምስት ተከታታይ ቀናት በተለያዩ ዝግጅቶች ሲካሄድ የቆየው 20ኛው የዓለም ሥራ ድርጅት አህጉራዊ ኮንፈረንስ  ተጠናቋል፡፡

በዛሬው ዕለት በተካሄደው መርሃ-ግብር ከሁለት ዓመት በኋላ አዘጋጅ የሆነችውን ሀገር ለመለየት በተደረገው የምርጫ ሂደት ለዕጩነት ከቀረቡት አምስት የአፍሪካ ሀገራት (ኬኒያ፣ ላይቤሪያ ፣ ቱኒዚያ ፣ ዛምቢያ እና ማዳጋስካር ) መካከል የደቡብ አፍሪካ ቀጠናዋ ሀገር ዛምቢያ የአሸናፊነቱን ዕድል አግኝታለች፡፡

እንደሚታወቀው የሌበር ቤዝድ ፕራክቲሽነርስ ኮንፈረንስ በዋናነት የሚያተኩረው ሀገራት በሚተገብሯቸው የተለያዩ የመሠረተ ልማት እና ሌሎች ፕሮግራሞች ወይም ፕሮጀክቶች እንዴት የሰው ኃይልን በስፋት መጠቀም እንደሚችሉ፣ እንዴት ዘላቂና ጥራት ያለው የሥራ ዕድል መፍጠር እንደሚቻል እንዲሁም በሂደቱ የሰራተኞችን ዘላቂ ተጠቃሚነት እና ደህንነት ማረጋገጥ የሚቻልባቸውን መንገዶች ታሳቢ በማድረግ ነው፡፡

ይህ ኮንፈረንስ በሁለት ዓመት አንድ ጊዜ የሚካሄድ አህጉራዊ ኮንፈረንስ ሲሆን በዋናነት በዓለም የሥራ ድርጅት (ILO) እና ኮንፈረንሱን እንዲያዘጋጅ በተመረጠው ሀገር መንግስት በጋራ የሚዘጋጅ ነው።

ለማስታወስ ያህል የመጀመሪያው ኮንፈረንስ የተካሄደው እ.ኤ.አ በ1990 በታንዛኒያ ነበር። ከዚህ በኋላ ከተካሄዱት 18 ኮንፈረንሶች መካከል የመጨረሻዎቹን አምስቱን ብንመለከት 15ኛው እ.ኤ.አ በ2014 በያውንዴ ካሜሩን፣ 16ኛው እ.ኤ.አ በ2015 በኮትኑ ቤኒን፣ 17ኛው እ.ኤ.አ በ2017 በአዲስ አበባ ኢትዮጵያ፣ 18ኛው እ.ኤ.አ በ2019 በቱኒዝ ቱኒዚያ እንዲሁም 19ኛው እ.ኤ.አ በ2023 በሩዋንዳ ኪጋሊ ነበር ። እንግዲህ ኢትዮጵያ 20ኛውን ኮንፈረንስ እንድታዘጋጅ በከፍተኛ ድምጽ የተመረጠችው በ2023 በሩዋንዳ ኪጋሊ በተካሄደው 19ኛው ኮንፈረንስ ወቅት ነበር።

ኢትዮጵያ 17ኛውን ዙር እ.ኤ.አ በ2017 በአዲስ አበባ አዘጋጅታ ለሁለተኛ ጊዜ 20ኛውን ዙር በድጋሜ የማዘጋጀት ዕድል ያገኘችው በትላልቅ ሀገራዊ ፕሮጀክቶች፣ በኮሪደር ልማት፣ በቤቶች ልማት እና ሰፋፊ የመንገድ እና ሌሎች መሠረተ ልማቶች ረገድ የሰራቻቸውን ስራዎችና ያስመዘገበቻቸውን ውጤቶች እንዲሁም ቀጣይ ትልሞቿን ግምት ውስጥ በማስገባት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ስለሺ ዘገዬ
የካሜራ ባለሙያዎች፡- አስመላሽ ተፈራ እና ፈዬ ደሜ

Posted in: News