
October 15, 2025
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 3/2018 ዓ.ም፣ (ከመልሚ) የከተማና መሠረተ-ልማት ሚኒስቴር አመራርና ሠራተኞች በሀገር ዓቀፍ ደረጃ ለ18ኛ ጊዜ “ሰንደቅ ፤ ለብሔራዊ አንድነታችን፤ ለሉዓላዊነታችን እና ለኢትዮጵያ ሕዳሴ!” በሚል መሪ ቃል የሚከበረውን የሠንደቅ ዓላማ ቀን በተለያዩ ዝግጅቶች በድምቀት አከበሩ፡፡
በዓሉ በተለያዩ ዝግጅቶች የተከበረ ሲሆን በዓሉን የሚዘክሩ የተለያዩ ጣዕመ ዜማዎች የቀረቡ ሲሆን በዓሉን እና ወቅታዊ ሀገራዊ ሁኔታዎችን በሚመለከት አጭር የውይይት ሠነድ ቀርቧል፡፡
የሠንደቅ ዓላማ ቀንን አስመልክቶ በሀገራችን የመጣውን ለውጥና የወደፊቱን ብሩህ ተስፋ የሚገልጽ የግጥም ጽሁፍ ከቀረበ በኋላ የኢትዮጵያ ህዝብ መዝሙር በፌደራል ፓሊስ የጸጥታ ኃይሎች ታጅቦ የመስቀል ሥነ-ስርዓት በጋራ የተካሄደ ሲሆን ባንዲራ ከመስቀል ሥነ-ስርዓት በኋላ ክብርት ሚኒስትር ወ/ሮ ጫልቱ ሳኒ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
በመልዕክታቸውም የኢትዮጵያ ሠንደቅ ዓላማ ምስጢር ጥልቅ የመሆኑን ያህል ኢትዮጵያ የሁላችንም ሀገር እንደሆነች ሁሉ በዜጎችና በሠንደቅ ዓላማ መካከል ያለው ግንኙነትም የህይወት ዋጋን እስከመክፈል የሚያደርስ የጠለቀ ምስጢር ያለው መሆኑን ገልጸዋል፡፡
አያይዘውም አሁን ያለንበት የማንሰራራት ዘመን ለዘመናት ተከማችቶ የነበረው ችግር እየተፈታ የመጣበትና በውጭና በውስጥ ሲሰራብን የነበረውን ደባ አሸንፈን የህዳሴያችንን ግድብ ዕውን ያደረግንበትና ሌሎች የልማት ስኬቶቻችንን ያረጋገጥንበት ዘመን በመሆኑ ባንዲራችን በዓለም አደባባይ ከፍ ብሎ እንዲውለበለብ የሀገራችን ገጽታ በከተማ ልማት ስራችን እንዲረጋገጥ የየበኩላችንን ያልተቆጠበ ጥረት ማድረግ ይጠበቅብናል ሲሉ ለመላ የሀገራችን ህዝቦችና ለተቋሙ ሠራተኞች የእንኳን ደስ አላችሁ የደስታ መግለጫ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
በመጨረሻም ዕለቱን የሚዘክሩ መልዕክቶች ተቀርጸው የአቋም መግለጫ ሆነው በቃለ-መሃላነት በጋራ ተላልፈዋል፡፡