
October 15, 2025
የኢትዮጵያ አስተማማኝነት እና ዘላቂነት ያለው የባህር በር የማግኘት ጉዳይ በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እያደገ የመጣ ቅቡልነት ማግኘት መቻሉን ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ ገለጹ።
6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና የፌዴሬሽን ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን የመክፈቻ ሥነ-ሥርዓት እየተካሄደ ይገኛል።
ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ በመክፈቻ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የመክፈቻ ንግግር እያደረጉ ይገኛል።
ፕሬዝዳንት ታዬ የውጭ ግንኙነት ማዕከል እና ማጥንጠኛው ብሄራዊ ጥቅም እና የዜጎች ክብር መሆኑን ገልጸዋል።
በዚህ መነሻነትም የኢትዮ ጂኦ ስትራተዌጂካዊ ቁመና በመደርጀት ላይ እንደሚገኝ ጠቅሰው ስትራቴጂ ምርጫው ኢትዮጵያን ከታዛቢነት ወደ አጀንዳ ተላሚነትና ተጽእኖ ፈጣሪነት ለማሸጋገር ማስቻሉን አመልክተዋል።
ኢትዮጵያ በድንበር ተሻጋሪ ሀብቶቿ ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ስታረጋገጥ በዛው አስተማማኝ የባህር በር ማግኘት እንደሚኖርባት ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ የህልውና መሰረት በሆኑ የውሃ ሀብቶች ላይ መንግስት ያልተቋረጠ ሰላማዊና ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶችን እያደረገ ይገኛል ብለዋል።
እስከ አሁን በተደረጉ ጥረቶች ሶስት ጉልህ ውጤቶች ተዘምግበዋል ነው ያሉት ፕሬዝዳንቱ።
የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት አጋጥመውት የነበሩትን ፈተናዎች በጥበብ በማለፍ ተጠናቆ ለምረቃ መብቃቱ ትልቁ ስኬት እንደሆነም ተናግረዋል።
አስተማማኝነት እና ዘላቂነት ያለው የባህር በር የማግኘት ጉዳይ ከፍ ወዳለ ደረጃ መሸጋገሩንና ይህ ፍትሃዊ ጥያቄ በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እያደገ የመጣ ቅቡልነት ማግኘት መቻሉን አመልክተዋል።
በሌላ በኩል በውጭ ሀገር ለእንግልት እና ለችግር የተጋለጡ ዜጎች በክብር ወደ ሀገር መመለሳችውንና ይህም በተጠናከረ መልኩ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።
መንግስት በውጭ ሀገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በሀገራቸው ጉዳይ ላይ ያላቸውን ተሳትፎ እንዲያድግ እየሰራ ነው ብለዋል።