(ፌ.ሥ.ፀ.ሙ.ኮ ታህሳስ 8/2017 ዓ.ም፣ አለም ገና) ለከተማና መሠረተ ልማት ዘርፍ አመራሮች “ሥነ-ምግባራዊ አመራርነት ለተቋማት ተልዕኮ ስኬት!” በሚል መሪ ቃል ስልጠና እየተሰጠ ነው።

በመድረኩ ዘርፉን ወክለው ንግግር ያደረጉት የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር መስፍን ነገዎ (ኢ/ር) የከተማና መሠረተልማት ዘርፍ በሀገር ደረጃ ግዙፍ የመንግስት እና የህዝብ ሀብት የሚንቀሳቀስበት በመሆኑ አመራሩ የላቀ ሥነምግባር ተላብሶ መምራት እንዳለበት አሳስበዋል።

የተበላሸ የአዕምሮ ውቅር ለብልሹ አሰራሮች መነሻ መሆኑን የጠቀሱት ዋና ዳይሬክተሩ፥ ችግሩን ለመቅረፍ የሥነምግባር ግንዛቤ ማሳደግና ሥልጠና ማስፋት አንዱ መሣሪያ መሆኑን አንስተዋል።

የኮሚሽኑ የሥነምግባር ግንባታ ዘርፍ ም/ኮሚሽነር ክቡር ፍቃዱ ሰቦቃ በበኩላቸው የፀረ-ሙስና ትግሉን ዘርፍ ተኮር በማድረግ ዘርፎች የፀረ-ሙስና ትግሉ ባለቤት እንዲሆኑ እየተሠራ መሆኑን ገልፀዋል።

ም/ኮሚሽነሩ አክለውም ዘርፍ ተኮር አሠራር ከጥናት ጀምሮ መካሂዱን በመጠቆም፥ ጥናቱን መሠረት ያደረጉ የሥልጠና ሞጁሎች በዩኒቨርሲቲ ምሁራን በማዘጋጀት ሥልጠና መሠጠት መጀመሩን ጠቅሠዋል።

በተጀመረው ሥልጠና የአመራር ሥነምግባር በመገንባት በዘርፍ ተቋማት ለፀረ-ሙስና ትግል አመቺ ሁኔታ እንደሚፈጠር ገልፀዋል።

ስልጠናው በዩኒቨርስቲ ምሁራን እየተሰጠ ሲሆን፥ ዛሬን ጨምሮ ለሁለት ቀናት የሚቀጥል ይሆናል።

ከሙስና የፀዳች እና የበለፀገች ኢትዮጵያን ዕውን እናድርግ

Posted in: Uncategorized