
June 11, 2025
ኮምቦልቻ፣ ግንቦት 27/2017 ዓ.ም (ከመልሚ) የከተሞች ልማታዊ ሴፍቲኔት እና የሥራ ፕሮጀክት የልምድ ልውውጥና የአውደ ጥናት መድረክ ላይ በክብር እንግድነት ተገኝተው የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የከተማና መሠረተ-ልማት ሚኒስቴር ሚኒስትር፣ ክብርት ወ/ሮ ጫልቱ ሳኒ ናቸው፡፡
እንደእርሳቸው ገለጻ የከተሞች ልማታዊ ሴፍቲኔት እና የሥራ ፕሮጀክት ከታለመለት ግብ አንጻር ተጨባጭ ለውጥ ያመጣ ፕሮጀክት ነው፡፡ ቀጣይነቱን ለማረጋገጥ ደግሞ አሰራርን በየጊዜው መፈተሽና ክፍተቶችን በጥናት እየለዩ አሠራሮችን ማሻሻልና በጎ ጎኖችን አጠናክሮ በማስቀጠል ለሚጠበቀው ውጤት ማብቃት እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡
ከዚሁ ጋር በማያያዝ ፕሮጀክቱ በጊዜ የተገደበ መሆኑን በማስታወስ የፕሮግራሙ ዓላማ ዜጎች ከተረጅነት ተላቀው ራሳቸውን እንዲችሉ ማድረግ ስለሆነ ለለውጥ በሚደረገው ጥረት የአካባቢ ልማት ስራዎች በዋነኛነት የተጠቃሚውን ህብረተሰብ እርካታ የሚያሳድጉ መሆን አለባቸው ብለዋል፡፡
ፕሮጀክቱ የከተማ ነዋሪውን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ተጠቃሚነት ያረጋገጠ እንዲሆን የተጠቃሚዎቻችን እርካታ ቁልፍ ጉዳያችን ሊሆን ይገባል ያሉት ክብርት ሚኒስትሯ የፕሮጀክቱ ውጤታማነት የሚለካው የተጠቃሚዎቹን ፍላጎት ማርካት ሲቻል ብቻ በመሆኑ ተጨማሪ ገቢን ለመሰብሰብ በከተማ ግብርና እና በሌሎች ተጨማሪ ገቢን በሚያስገኙ ስራዎች ላይ ማሳተፍና በቅሬታ አፈታት ላይ ትኩረት ሰጥቶ መስራት ይገባል ብለዋል፡፡
የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት ያስተላለፉት የኮምቦልቻ ከተማ ከንቲባ አቶ መሀመድአሚን የሱፍ በበኩላቸው የኮምቦልቻ ከተማ ከተመሰረተችበት ከ1928 ዓ.ም ጀምሮ የኢንዱስትሪ ከተማ እንደነበረች በመግለጽ አሁን ላይ 127 በስራ ላይ ያሉ ፋብሪካዎችና 110 በግንባታ ሂደት ላይ የሚገኙ ፋብሪካዎች በከተማዋ እንዳሉ እና ከተማዋን የኢንቨስትመንትና የኢንዱስትሪ መዳረሻ ለማድረግ እየሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
የመክፈቻ ፕሮግራሙን ተከትሎ በመድረኩ ስኬታማ የሆኑና በተደረገላቸው ድጋፍ ህይወታቸውን የቀየሩ የፕሮጀክቱ ተጠቃሚዎች ተሞክሮ ቀርቧል፡፡ ከዚያም በኮምቦልቻ ከተማ የአካባቢ ልማት ስራዎች ጉብኝት የተደረገ ሲሆን በአካባቢ ልማት የሳይት ኦዲት ላይ የተካሄደ የዳሰሳ ጥናትና በኑሮ ማሻሻያ አተገባበር ላይ የተካሄደ የዳሰሳ ጥናት እና የቅሬታና አቤቱታ አፈታት ላይ የተካሄደ የዳሰሳ ጥናት፤ በከተማ ግብርና አተገባበር ላይ የተቀመረ የተሞክሮ ሰነድ እና በJERIS ስምምነት የተደረሰባቸው ቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎችን የተመለከተ ሠነድ ቀርቧል፡፡
ሪፖርተር፡- ስለሺ ዘገዬ
የካሜራ ባለሙያ ፡- አስመላሽ ተፈራ