
June 24, 2025
አዳማ፣ ሰኔ 13 ቀን ፣ 2017 ዓ.ም (ከ.መ.ል.ሚ)፡- የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪውን አስመልቶ አዲስ በተዘጋጀ የቁጥጥር ረቂቅ ደንብ ዙሪያ ከክልል አመራች እና ከባለድርሻ አካላት ጋር የውይይት መድረክ በአዳማ ከተማ ተካሂዷል፡፡
ረቂቅ ደንቡን ያቀረቡት በከተማና መሠረተ-ልማት ሚኒስቴር የኮንስትራክሽን መሠረተ-ልማት መሪ ስራ አስፈጻሚ ወ/ሮ መዲና አህመድ ደንቡ በፌደራል፣ በክልሎች እና በከተማ አስተዳደሮች ተፈጻሚነት እንደሚኖረው ገልጸዋል።
በማንኛውም የኮንስትራክሽን ፕሮጀክቶች፣ በግንባታ ባለቤቶች፣ በስራ ተቋራጮች፣ በአማካሪዎች፣ በተዛማጅ ስራዎች ላይ በተሠማሩ ባለሙያዎች እና ድርጅቶች ተፈጻሚ እንደሚሆን ወ/ሮ መድና ተናግረዋል፡፡
በደንቡ ከተካተቱት ዋና ጉዳዮች የስራ ቦታ ደህንነትን በሚመለከት አንድ ፕሮጀክት ከአንድ ዓመት በላይ የቆይታ ጊዜ ካለው የግናባታ ፕሮጀክቱ የውል ዋጋ 30 ሚሊዮን ብር በላይ ከሆነ፣ ተጋላጭነቱ ከፍተኛ ከሆነ እንዲሁም በሀገር ደህንነት ጋር በተያያዘ በሚኒስትሮች ምክር ቤት በሚወሰኑ ድንጋጌዎች መሠረት ተፈጻሚ እንደሚሆን ወ/ሮ መዲና ገልጸዋል ፡፡
ሃላፊዋ አያይዘው ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በዚህ ደንብ ላይ የሚኖረው ተግባርና ሀላፊነት አስፈጻሚ አካላት የአጭር፣ የመካከለኛ እና የረጅም ጊዜ ዕቅዳቸውን በማዘጋጀት በተቀናጀ ሀገራዊ የመሠረተ-ልማት ማስተር ፕላን እንዲካተት በማድረግ እና ከዚያም አልፎ ተቋማቱ ዕቅዳቸውን አጸድቀው ወደ ተግባር እንዲገቡ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል ብለዋል፡፡
በመጨረሻም ደንቡ ኃላፊነትን፣ ተጠያቂነትና እና ግዴታዎችን እንዴት መወጣት እንደሚቻል በግልጽ የሚያመላከት መሆኑን ተሳታፊዎች ገልጸው መስተካከል የሚገባቸው ነጥቦች ተጨምረው በአጭር ጊዜ ጸድቆ ወደስራ እንዲገባ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡
ሪፖርተር፡-ሞገስ ዓሊ
ፎቶግራፍ ፡- አስመላሽ ተፈራ