August 13, 2025

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 6፣ 2017 (ከመልሚ)
የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር የኮንስትራሽን እንዱስትሪ ዘርፍ ወደ አዲስ ከፍታ ለማሸጋገር በፈረንጆቹ ከ2025 እስከ 2050 ድረስ የሚተገበር የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ትራንስፎርሜሽን ኢኒሼቲቭ ይፋ ማድረጊያ መረሃ-ግብር ዛሬ ተካሂዷል።

ክቡር ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በመረሃ-ግብሩ ላይ እንዳሉት፤ መንግሥት ለዚህ የልዕልና ህልም መሳካት ኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪውን ጨምሮ ብሔራዊ የልማት ዕቅዶችን እየተገበረ ይገኛል።

ኢኒሼቲቩ ዘመናዊ፣ ተወዳዳሪ እና ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ለመፍጠር እንደሚያስችል ገልጸው፤ ቁልፍ ሀገራዊ የኮንስትራክሽን ተግዳሮቶችን ጭምር በጋራ የሚፈታም ነው ብለዋል።

በተጨማሪም ኢኒሼቲቩ ቅንጅትን የሚያጠናክር፣ የኢትዮጵያ ኩባንያዎች በአፍሪካ አሻራቸውን እንዲያሳርፉ ምቹ ሁኔታ የሚፈጥር፣ በአፈጻጸም ላይ የተመሰረተ የምዘና፣ የእውቅና እና የተጠያቂነት አሰራርን በመዘርጋት በዘርፉ ተወዳዳሪነትን የሚያመጣ መሆኑን ተናግረዋል ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ።

የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስትር ክብርት ጫልቱ ሳኒ በበኩላቸው ኢኒሼቲቩ ተግባራዊ ሲደረግ በዘርፋ የሚስተዋለውን ብልሹ አሰራር በቀላሉ ለመቆጣጠር ያስችላል ብለዋል።

የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው በርካታ አምራች የሰው ሀይልን የሚፈልግ እንደመሆኑ መጠን ለስራ አጥ ዜጎች ተጨማሪ የስራ እድልን ለመፍጠር አቅም እንደሚኖረው የተናገሩት ክብርት ሚኒስትር ፤ ኢንሼቲቩ ከውጭ የሚገቡ ግብአቶችን በሀገር ውስጥ በመተካት ለግዥ ይወጣ የነበረውን የውጭ ምንዛሬ በማስቀረት ረገድ ጉልህ ድርሻ አለው ብለዋል።

በቀጣይ ዓመታት በርካታ   ብቁ  የአገር ውስጥ ተቋራጮችን በማብቃት ከአገር ውስጥ በተጨማሪ በለሎች አገራት በግንባታው ዘርፍ የሚሰማሩበትን አቅም እንዲያዳብሩ እንደምሰራ ክብርት ሚኒስትር ተናግረዋል።

Posted in: News