ጥር 15, 2026
አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 23፣ 2018 (ከመልሚ)
የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር የመንግሰት አገልግሎት እና አስተዳደር ሪፎርም ስራዎችን አስመልክቶ ከተለያዩ የከፍተኛ የትምህርት እና ስልጠና ተቋማት ጋር በጋራ ለመስራት የመግባቢያ ስምምነት ሰነድ ተፈራርሟል፡፡
ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የተለያዩ አደረጃጀቶችን በመፍጠር የመንግስት አገልግሎት እና አስተዳደር ሪፎርም የዝግጅት ምእራፍ ስራዎችን እያከናወነ ሲሆን በተለይ በሰው ኃይል ብቃትና ምዘና ሥርዓትን በብቃት ለመወጣት ነው ከመንግሰት ከፍተኛ የትምህርት እና ስልጠና ተቋማት ጋር የመግባቢያ ስምምነት ሰነድ የተፈራረመው ፡፡
ተቋማቱም የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ፣ የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲ፣ የኢትዮጵያ ፐብሊክ ሰርቪስ ዩኒቨርስቲ፣ የኢትዮጵያ ብቃትና ሥራ አመራር ኢንስቲትዩት ፕሬዝደንቶች ከሚኒስቴር መ/ቤቱ በኩል ክቡር ሚኒስተር ድኤታ የትምጌታ አስራት(ዶ/ር) ሲሆኑ ኢፊዲሪ ቴክኒክና ሙያ ስልጠና ኢንስቲትዩት በቀጣይ ከሚኒስቴር መ/ቤቱ ጋራ ለመስራት የመግባቢያ ሰነዱን ይፈራረማሉ ተብሎ ይጠበቃል ፡፡
የፊርማ ስነ-ስርዓቱን አስመልክቶ መልዕክት ያስተላለፉት የከተማና መሠረተ-ልማት ሚኒስቴር ሚኒስትር ክብርት ወ/ሮ ጫልቱ ሳኒ እንደተናገሩት የመንግሰት አገልግሎት እና አስተዳደር ሪፎርም ውጤታማነት ከባለድርሻ አካላት ጋር ተቀናጅቶ መሥራት ፋይዳው የጎላ መሆኑን ገልጸው ሪፎርሙ ከተለመደው ኋላቀር-አሠራር በመውጣት ዘመኑ የሚጠይቀውን በድጅታል ቴክኖሎጂ በመታገዝ ዜጎች ለሚያነሷቸው ጥያቄዎች ፈጣንና ቀልጣፋ እንዲሁም እርካታን የሚያጎናጽፉ የአሠራር ሥርዓቶችን ለመዘርጋት ነዉ ብለዋል።
የከፍተኛ ትምህርት እና ስልጠና ተቋማቱ ኃላፊነት የሞጁል ዝግጅት፣ የካሪኩሌም ዝግጅት፣ የሰው ኃይል ብቃትና ምዘና፣ ተከታታይ ስልጠናዎችን፣ የምዘናና ውጤት የመግለጽ ስራዎችን ለማከናወን እንደሆነ በፊርማ ስነ-ስርዓቱ ተመልክቷል፡፡
የከፍተኛ የትምህርት እና ስልጠና ተቋማት የስራ ሀላፊዎች በበኩላቸው የተጣለባቸው ኃላፊነት የትውልድ አደራ በመሆኑ በአግባቡ ሠርተው ለሪፎርሙ ስከት የበኩላቸውን ሚና እንደሚወጡ ገልጸዋል፡፡