
ሐምሌ 1, 2025
መቀሌ፣ ሰኔ 17/2017 ዓ/ም (ከመልሚ)
ከጊዜ ወደጊዜ እያደገ የመጣውን የህዝብ ቁጥር ፍላጎት ለማሟላት በቤት ልማትና አስተዳደር ዙሪያ መንግስት ዘርፈ-ብዙ ስራዎችን በመስራቱ ተጨባጭ ውጤቶች መመዝገባቸው ተገለጸ፡፡
መንግስት የዜጎች መሠረታዊ መብት የሆነውን የቤት ቅርቦት በማሻሻል የሚታየውን የአቅርቦትና የፍላጎት አለማጣጣም ችግር በዘላቂነት ለመፍታት የቀረጻቸውን ፖሊሲና ስትራቴጂዎች ተከትለው ከወጡ አዋጆች መካከል በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጸደቀው የመኖሪያ ቤት ኪራይ ቁጥጥር እና አስተዳደር አዋጅ ቁጥር 1320/2016 እና በሪል እስቴት እና በቋሚ ንብረት ግመታ አዋጅ ቁጥር 1357/2017 የወጣው አዋጅ ይገኙበታል፡፡
መንግስት የተለያዩ ፕሮጀክቶችንና ፕሮግራሞችን ቀርጾ የፖሊሲ ለውጥ በማምጣትና የግሉን ዘርፍ ተሳትፎ በማሳደግ በተሰሩ ስራዎች ተጨበጭ ውጤቶች መመዝገባቸውን የገለጹት በከተማና መሠረተ-ልማት ሚኒስቴር የቤቶች ልማት መሪ ስራ አስፈጻሚ ወ/ሪት ትዕግስት ዓለሙ ናቸው፡፡
ስራ አስፈጻሚዋ ይህን የተናገሩት በትግራይ ክልል ለሚገኙ የክልል፣ የዞንና የከተማ ልማት ዘርፍ አመራርና ባለሙያዎች በመቀሌ ከተማ ሰኔ 17/2017 ዓ.ም በተዘጋጀው ክልል አቀፍ የአቅም ግንባታ የስልጠና መድረክ መክፈቻ ላይ ነው፡፡
ስልጠናው በዋናነት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በጸደቀው የመኖሪያ ቤት ኪራይ ቁጥጥር እና አስተዳደር አዋጅ፤ በቤት ልማት መሪ ዕቅድና ስትራቴጂ እንዲሁም በሪል እስቴት አዋጅና ደንብ ላይ ትኩረቱን ያደረገ ነው ያሉት ዋና ስራ አስፈጻሚዋ የተዘጋጀው መድረክ የክልሉን የመፈጸም አቅም ለማሳደግ ያለመ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
በመድረኩ ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ምክትል ፕሬዚዳንትና የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ ኃላፊው ክቡር አቶ አማኑኤል አሰፋ በበኩላቸው የኪራይ ቤት አዋጅ መውጣቱ በኪራይ ቤት የሚኖሩ ዜጎች በህግ እንዲደገፉ በማድረግ በአከራይና ተከራይ መካከል ያለው ግንኙነት ጤናማና ህጋዊ ስርዓትን የተከተለ እንዲሆን ከማድረጉ ባሻገር የመንግስትን ገቢ ለማሳደግ እንደሚረዳ ነው ብለዋል፡፡ ለስልጠና የተዘጋጁት የህግ ማዕቀፎችም በጦርነት የተጎዳውን ክልል መልሶ ለመገንባትና የክልላቸውን ሠላም ለማስከበር ከማገዙም በላይ የነዋሪዎችን ጥያቄ ለመመለስ የሚያስችል እንደሆነም ገልጸዋል፡፡
ለስልጠናው የተዘጋጁት ሠነዶች በስራ አስፈጻሚው የዴስክ ኃላፊዎች በአቶ ታፈሰ ነጋ እና በአቶ በላይ ካህሳይ የቀረቡ ሲሆን በተደረገው የጋራ ውይይት የአከራይ ተከራይ አዋጁ የጋራ ጥቅምን ለማስከበር ያለመ መሆኑ ላይ የጋራ ግንዛቤ ተይዞ ሌሎች ጉዳዮችን በተመለከተ የገጠር ማዕከላት ግንባታ፣ የግሉ ዘርፍ ተሳትፎ፣ የማህበራት ቤት ግንባታ፣ የስማርት ሲቲ ግንባታ፤ የቤቶች መረጃ አያያዝ (ለዚሁ ዓላማ በተዘጋጀው ሶፍትዌር የማስገባት ስራ) እና መሰል ጉዳዮች በክልሉ ያሉበት ተጨባጭ ሁኔታ በጋራ ውይይት የተገመገሙ ሲሆን በሪል እስቴት ለሚሰማሩ ኩባንያዎች ቀደም ሲል መሬት ይተላለፍበት ከነበረው የምደባ እና የሊዝ አማራጭ በተጨማሪ በድርድር የሚቀርብበት ዕድል መኖሩ ለሪል እስቴት አልሚዎች መልካም አጋጣሚ እንደሆነና አዋጁም የሪል እስቴት ዘርፉ በስርዓት እንዲመራ የሚያግዝ እንደሆነ ተወስቷል፡፡
በመጨረሻም በውይይቱ ማጠቃለያ ላይ በ2016 ዓ.ም ጸድቆ ወደስራ የገባው የአከራይ ተከራይ አዋጁ ምንም እንኳ ከጸደቀበት ጊዜ ጀምሮ በአዲስ አበባና በብዙ የሀገሪቱ ክልሎችና ከተሞች የተተገበረ ቢሆንም በትግራይ ክልል በነበረው ሁኔታ አዋጁን ተግባራዊ ማድረግ ያልተቻለ ቢሆንም በተሰጠው የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና የአዋጁን መንፈስ በጥልቀት በመረዳት፤ የአዲስ አበባን ተሞክሮ በመውሰድ፤ በከተማና መሠረተ-ልማት ሚኒስቴር የተዘጋጀውን ሞዴል መመሪያ ከክልሉ ተጨባጭ ሁኔታ ጋር በማዛመድ በተዘጋጀው መመሪያ መሠረት በ2018 በጀት ዓመት ወደስራ ለመግባት ዝግጁ መሆናቸውን የክልሉ ከተማና ኮንስትራክሽን ቢሮ ኃላፊዎችና ከዞንና ከከተሞች በስልጠናው የተሳተፉ አመራርና ባለሙያዎች ተናግረዋል፡፡
ሪፖርተር፡- ስለሺ ዘገዬ
የካሜራ ባለሙያ፡- ፈዬ ደሜ