ታህሳስ 12, 2025

አዲስ አበባ፣ ህዳር 24 ቀን፣ 2018 ዓ.ም (ከ.መ.ል.ሚ)

አስረኛው የኢትዮጵያ ከተሞች ፎረም በስኬት መጠናቀቁን አሰመልክቶ የምስጋናና የዕውቅና መርሃ-ግብር በከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር ተካሄዷል፡፡

የምስጋናና የዕውቅና መረሀ ግብሩ በተለያዬ ደረጃ ለፎረሙ መሳካት የራሳቸውን ድርሻ ላበረከቱ ተቋማትና ግለሰቦች ነው የተሰጠው።

የክልሉ ፕሬዝዳንት ክቡር አቶ ሐጂ አዎል አርባ በሰጡት አመራር በየደረጃው የሚገኙ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮችና ባለሙያዎች እንዲሁም የክልሉ መላው ህብረተሰብ አስረኛውን የኢትዮጵያ ከተሞች ፎረም ለማዘጋጀት ባደረጉት ከፍተኛ ጥረት ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከፍተኛ ምስጋና አቅርቧል፡፡

በተለይ አስረኛውን የኢትዮጵያ ከተሞች ፎረም በተሳካ መንገድ  ላዘጋጀው ለአፋር ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ሰመራ-ሎግያ ከተማ በኤሌክትሪክ ሀይል የሚሰራ ተሽከርካሪ ከከተማና መሠረተ-ልማት ሚኒስቴር ተበርክቶላቸዋል፡፡

አስረኛው የኢትዮጵያ ከተሞች ፎረም በተለየ መንገድ ልምድ፣ ተሞክሮዎች እና አዳዲስ የቴክኖሎጂ ውጤቶች/ዲጂታላይዜሽን/ አሰራሮች በበርካታ ከተሞች በመተግበር የከተማ ነዋሪዎችን ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት እየተሰጠ እንደሚገኝ የታየበት እንደነበር የከተማና መሠረተ-ልማት ሚኒስቴር ሚኒስትር ክብርት ወ/ሮ ጫልቱ ሳኒ ሽልማቱን በሰጡበት ወቅት ተናግረዋል፡፡

ቀጣዩን አስራ አንደኛውን የኢትዮጵያ ከተሞች ፎረም የሚያዘጋጀው የቤኒሻንጉል ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት የአሶሳ ከተማ ከአስረኛዉ የኢትዮጵያ ከተሞች ፎረም እና ካለፉት ፎረሞች ልምድ በመውሰድ ዝግጅት እንዲያደርግ በመድረኩ ተገልጿል፡፡

Posted in: ዜና