ሰኔ 25, 2025

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 17 ቀን 2017 ዓ.ም (ከመልሚ) ዓለም አቀፉ የ”ቢግ-5 ኮንስትራክት ኢትዮጵያ” የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ኤግዚቪሽን፣ ሲምፖዚየም እና የንግድ ትርኢት ከሰኔ 19-21/2017 ዓ.ም በአዲስ አበባ ሚሊኒየም አዳራሽ ይካሄዳል።

ቢግ-5 በየዓመቱ በዱባይ የተባበሩት አረብ ኢሚሬቶች፣ በመካከለኛው ምስራቅ፣ አፍሪካ እና ደቡብ እስያ  አህጉሮች ውስጥ ትልቁ እና ከፍተኛው የኮንስትራክሽን ሁነት ነው።

በዱባይ የዓለም የንግድ ማዕከል የተካሄደው ግዙፉ የቢግ-5 ሁነት ከ85,000 በላይ ተሳታፊዎችን ከ165 በላይ ሀገራትን በመሳብ በሺህ የሚቆጠሩ ምርቶችን እና ፈጠራዎች የሚቀርቡበት ትልቅ አለም አቀፍ ሁነት ነው፡፡

ሁነቱን በሚመለከት ጋዜጣዊ መግለጫ የሰጡት የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስትር ክብርት ወ/ሮ ጫልቱ ሳኒ እንደተናገሩት “ቢግ-5 ኮንስትራክት ኢትዮጵያ” የሀገር ውስጥ እና አለም አቀፍ የኮንሰትራክሽን ኢንዱስትሪ ተዋናዎች፣ የፈጠራ ባለቤቶች እና የግንባታ ግብአት አቅራቢዎች የሚሰባሰቡበት ሁሉን አቀፍ መድረክ በመሆኑ የኮንስትራክሽን ዘርፉን በከፍተኛ ሁኔታ ያሳድጋል።

በኤግዚቢሽኑ ከግንባታ እቃዎች እና ማሽነሪዎች እስከ ዲጂታል የግንባታ ቴክኖሎጂዎች እና ዘላቂ መፍትሄዎች ሰፊ ምርቶችን እና አገልግሎቶች ይቀርቡበታልም ብለዋል ክብርት ሚኒስትሯ፡፡

መድረኩም የአገር ውስጥ የዘርፉ ተዋናዎች አዳዲስ ፈጠራዎች እና ልምዶች እንድቀስሙ፣ የቴክኖሎጂ እድገቶችን እና የአሰራር ስርአቶችን እንዲገበዩ እንደሚያግዝም ገልጸዋል ።

ለሶሶስተኛ ጊዜ የሚካሄደው “ቢግ-5 ኮንስትራክት ኢትዮጵያ” ሁነት ከ20 በላይ ሀገራት 127 አለም አቀፍ እና 39 የሀገር ውስጥ የዘርፉ ኩባንያዎች በኤግዚቢሽን እንደምሳተፉም ተናግረዋል።

በተጨማሪም ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች በፍጥነት በማደግ ላይ ያለውን የኢትዮጵያ የኮንስትረክሽን ገበያ ውስጥ  የመግባት ዕድል እንድያገኙ ምቹ ሁነታን እንደሚፈጥር ይታመናል ብለዋል።

ለአለም አቀፍ ኩባንያዎች  ተሳትፎ ዘለግ ላለ ጊዜ የሚቆዩ የኢንቨስትመንት እድሎችን ይፈጥራል፣ ይህ ደግሞ በኢትዮጵያ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ላይ ተከታታይ ፈጠራዎችን አና የሥራ እድሎችን እንደምፈጥርም ገልጸዋል ክብርት ሚኒስትር በመግለጫው ።

በመድረኩም የሀገራችን የተትረፈረፈ የተፈጥሮ ሃብት፣ በፍጥነት እያደገ ያለው ኢኮኖሚ፣ ወጣት እና የተማረ የሰው ሃይል እና ሰፋፊ መሠረተ ልማት ዝርጋታ ላይ ጉልህ እድሎችን ሀገራችን ይዛ እንደምትቀርብ ገልጸዋል።

ሁነቱን የከተማና መሠረተ-ልማት ሚኒስቴር ከዓለም አቀፉ DMG ኢቨንትስ እና ኢትኤል ኢቨንት እንዲሁም የዝህ ዝግጅት ስትራቴጂክ አጋር ከሆነው የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽን ጋር በጋራ አዘጋጅተዋል።

ፎቶግራፍ -አስመላሽ ተፈራ

Posted in: ዜና