ታህሳስ 22, 2025
አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 7/2018 ዓ.ም፣ (ከመልሚ)
በከተማና መሠረተ-ልማት ሚኒስቴር አማካኝነት በተዘጋጀ ረቂቅ የቤት ልማት ፖሊሲ ሠነድ ላይ አነስተኛና መካከለኛ ገቢ ያላቸው ዜጎችን የቤት ፍላጎት ለማሟላት በተካተተ የቤት ልማት ፕሮግራም ከሪል እስቴት አልሚዎች ጋር የሚመክር የግብዓት ማሰባሰቢያ መርሃ-ግብር በአዲስ አበባ ስካይላይት ሆቴል ተካሄደ፡፡
መድረኩን በንግግር ያስጀመሩት ክብርት ሚኒስትር ወ/ሮ ጫልቱ ሳኒ በመክፈቻ ንግግራቸው እንዳሉት ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ (ዶ/ር) ታላቁን የህዳሴ ግድብ ግንባታ ባስመረቁበት ወቅት በይፋ እንደተናገሩት የ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ቤቶች ግንባታን በቀጣዮቹ 5 ዓመታት ዕውን ለማድረግ የተያዘውን ዕቅድ ተግባራዊ ለማድረግ የተዘጋጀ ረቂቅ ፖሊሲ እንደሆነ ገልጸው ከአሁን በፊት የቤት ልማት ፖሊሲ እንዳልነበረና የቤት ልማቱ እንደ አንድ ፕሮግራም የተያዘ እንደነበር ገልጸው መድረኩ ግብኣት ለማሰባሰብና ረቂቅ ፖሊሲውን ለማዳበር ያለመ እንደሆነ በማስታወስ ለዕቅዱ ዕውን መሆን የግሉ ዘርፍ ተሳትፎ የማይተካ ሜና ስላለው ተሳታፊዎች ያልተገደበ አስተያየታቸውን እንዲሰጡ ጋብዘዋል፡፡
የመክፈቻ ንግግሩን ተከትሎ የተዘጋጀውን ረቂቅ ሠነድ ያቀረቡት በከተማና መሠረተ-ልማት ሚኒስቴር የቤቶች ልማት መሪ ስራ አስፈጻሚው አቶ ፀጋዬ ሞሼ የፖሊሲውን ዝርዝር ጉዳይ ሲያቀርቡ እንደተናገሩት ዝቅተኛና መካከለኛ ገቢ ላላቸው ዜጎች የመኖሪያ አቅርቦትን ተደራሽ ለማድረግ 8 የፖሊሲ አቅጣጫዎችን ለይቶ ያስቀመጠ እንደሆነና የቤት ልማት ፋይናንስን፣ የመሬት አቅርቦትን፣ አቅም ያገናዘበ ቤት መገንባትን፣ ዘመናዊ ቴክኖሎጂ መጠቀምን፣ የገጠር ቀበሌዎችንና ሁለተኛ ከተሞችን ታሳቢ ያደረገ መሆንን፣የመሠረተ-ልማት መሟላትን፣ የቤት ፈላጊዎችን የተጠናከረ መረጃ መያዝን እና ጠንካራ የቤት አቅርቦት ግብይት ስርዓትን ያካተተ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
አያይዘውም የፖሊሲው ዓላማ ተገማችና ብቁ የቤት አቅርቦትን 91 በመቶ ለሚሆነው ዝቅተኛና መካከለኛ ገቢ ላለው የህብረተሰብ ክፍላችን ተደራሽ ለማድረግ ያለመ እንደሆነና የሚገነቡት ቤቶችም በ5 የቤት ልማት አማራጮች እንደሚገነቡና የተለያዩ የቴክኖሎጂ አማራጮችን ተጠቅሞ በተዘጋጀው ዲዛይን መሠረት ግንባታው የሚከናወን እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
በተደረገው የጋራ ውይይት በርካታ ግብዓቶች የተገኙ ሲሆን የፖሊሲው በአጠረ-ጊዜ እንዲህ በተደራጀ መልኩ ተዘጋጅቶ መቅረቡና የግል ባለሀብቱን ሚና ያጎላ መሆኑ፣ የፋይናንስ ምንጮችም ተለይቶ የሚቀርብበት ዕድል መፈጠሩ እና የግል ባለሀብቱ አቅሙን አቀናጅቶ እንዲጠቀም ዕድል መስጠቱ የሚበረታታና አስደሳች መሆኑን አድንቀው የበኩላቸውን ድርሻ ለመወጣት ዝግጁ መሆቸውን ገልጸዋል፡፡
በመጨረሻም መድረኩን የመሩት ክቡራን ሚኒስትር ዴኤታዎች በሰጡት የማጠቃለያ አስተያየት መርሃ-ግብሩ የተጠናቀቀ ሲሆን ክቡር የትምጌታ አስራት (ዶ/ር) የተነሱ ነጥቦች ሁሉ ጠቃሚዎችና ፖሊሲውን ለማዳበር የሚያስችሉ መሆናቸውን ገልጸው በግንባታው ሂደት የምንፈጥረው አቅም በጣም ከፍተኛና ከቤት ግንባታ ባለፈ ለሀገር ግንባታው ከፍተኛ አስተዋጽኦ ሊያበረክት የሚችል እንደሆነም ተናግረዋል፡፡
ክብርት ወ/ሮ ሔለንም በበኩላቸው የፕሮጀክቱ ሌጋሲ ከሀገርና ከህዝብ ዕድገት ጋር የሚቀጥል እንደሆነ ገልጸው የቴክኖሎጂውን ችግር በመፍታት የህብረተሰቡን ችግር መፍታት እንደሚቻል ተናግረው ሀገርን በዘላቂነት መገንባት ለግል ሴክተሩ የተሰጠ ኃላፊነት ነውም ብለዋል፡፡