ሐምሌ 7, 2025

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 24/2017 ዓ.ም፣ (ከመልሚ) የኮንስትራክሽን ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት የሀገሪቱን የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ዘርፍ አቅም ለመገንባት የሚያደርገውን ከፍተኛ ጥረት ለማገዝ የኮንስትራክሽን ስራዎች የምክር አገልግሎት የክፍያ ሰነድ (Best Practice Construction Consultancy Fee Guideline) ለማዘጋጀት ከኢትዮጵያ አማካሪ መሃንዲሶችና አርክቴክቶች ማህበር ጋር በተገባው የምክር አገልግሎት ውል መሠረት ማህበሩ የተጣለበትን ኃላፊነትና አደራ ለመወጣት ቀዳሚ ጥናቱን ካከናወነው ሀብኮን ኮንሰልት አማካሪ ድርጅት ጋር ውል በመፈራረምና የጥናቱንም ሂደት በኢንስቲትዩቱ ባለሙያዎችና በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ጣምራ ቁጥጥርና በማህበሩ ተወካይ የቦርድ አባላት ክትትል እና ድጋፍ ኢንስቲትዩቱ ባስቀመጠው የውል አቅጣጫ መሠረት  ጥናቱ እንዲካሄድ አስፈላጊውን ክትትልና ቁጥጥር ሲያደርግ ቆይቷል፡፡

ጥናቱን ለማጠናቀቅ እና ቀደም ሲል በሰነዱ የተሰጡ አስተያየቶችና ትችቶችን በማካተት ዳብሮ በተሻሻለው ሰነድ ላይ ሁሉን አካታች የሆነ ተጨማሪ የማጠናከሪያ ግምገማና  ግብአቶችን ለመሰብሰብ የሚያስችል የአውደ-ጥናት መድረክ በዛሬው ዕለት ተካሄዷል፡፡

በመድረኩ የመክፈቻ ሥነ-ስርዓት ላይ የተገኙት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የከተማ፣ መሠረተ ልማትና ትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ም/ሰብሳቢ የተከበሩ እሸቱ ተመስገን (ዶ/ር) ለብዙ ዓመታት ችግር ውስጥ የነበረውን የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ዘርፍ ለመታደግ ከፍተኛ ደስታ የሚገኘው ለሙያው ክብር በመስጠት ከግል ጥቅም  ይልቅ ሀገርንና ህዝብን ማዕከል ያደረገ የሙያ ስራ በመስራት የኢንዱስትሪውን ትንሳኤ ማረጋገጥ ይገባል ብለዋል፡፡

የከተማና መሠረተ-ልማት ሚኒስቴር የመሠረተ-ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አቶ የትምጌታ አስራት በበኩላቸው የምንሰራው ስራ ሁሉ ከሀገር ግንባታ ጋር የተገናኘ ስለሆነ ለኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው የተሰጠውን ግልጽ ተልዕኮ ለመፈጸም ስራችንንን በጥራት፣ በብቃት እና በታማኝነት በማከናወን ሀገራችንን በመደመር እሳቤ በጋራ እንገንባ! በዚህ እሳቤ የተቃኘ የተግባር መነሳሳት ወሳኝነት አለው ብለዋል፡፡

ለዚህም የዘርፉን የቆየ ትርክት በመለወጥ ዘርፉን ለማሻገር ችግሩን በልኩ ተገንዝቦ መውጫ መንገዱን ማዘጋጀት ከመድረኩ ተሳታፊዎች ይጠበቃል፡፡ ስለሆነም ኢንዱስትሪው ለስራው በሚመች ከባቢ ውስጥ መገኘት ስላለበት የግሉ ዘርፍ ከመንግስት አካሉ ጋር ተቀናጅቶ በመስራት የሚፈለገውን ለውጥ ለማምጣት በጋራ መረባረብ ይኖርበታል ብለዋል፡፡

የመክፈቻ ንግግሩን ተከትሎ በመድረኩ ላይ በአማካሪ ድርጅቱ የተጠናው ጥናትና በከተማና መሠረተ-ልማት ሚኒስቴር በኩል የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ትራንስፎርሜሽን ኢኒሸቲቭ እና ሚኒስቴር መ/ቤቱ በቅርቡ ያጸደቃቸው የኮንስትራክሽን ዘርፍ አዋጆች፣ መመሪያዎችና የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ፖሊሲን የተመለከቱ ሠነዶች በሚኒስቴር መ/ቤቱ የስራ ኃላፊዎች ለአውደ-ጥናቱ ተሳታፊዎች ቀርበዋል፡፡

በአውደ ጥናት መድረኩ ላይ የቋሚ ኮሚቴው ም/ሰብሳቢን ጨምሮ የሚኒስቴር መ/ቤቱና የተጠሪ ተቋማት ከፍተኛ አመራሮችና የስራ ኃላፊዎች፣ የማህበሩ አባላት፤ አባል ያልሆኑ የአማካሪ መሃንዲሶችና አርክቴክቶች፤ የሙያ ማህበራት አመራሮች፤ ባለድርሻ አካላትና የመንግስት የስራ ኃላፊዎች እንዲሁም የዩኒቨርሲቲ ምሁራን የተገኙ ሲሆን ገለጻና ማብራሪያውን ተከትሎ  በተደረገው የጋራ ውይይት ጥናቱን ለማዳበር የሚያስችሉ በርካታ ግብአቶች ተገኝተዋል፡፡

ከመድረኩ ጎን ለጎንም ስፖንሰር አድራጊዎች ምርትና አገልግሎታቸውን ለማስተዋወቅ ያዘጋጇቸው ዲስፕሌዮች የተጎበኙ ሰሆን በአውደ-ጥናቱ ማጠቃለያ ላይም ለእነዚሁ ተባባሪ አካላት የእውቅና እና የምስጋና የምስክር ወረቀት ተበርክቶላቸዋል፡፡ 

ሪፖርተር፡- ስለሺ ዘገዬ
ፎቶግራፍ ፡- አስመላሽ ተፈራ

Posted in: ዜና