ሚያዝያ 2, 2026
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 23 ቀን 2018 ዓ.ም (ከመልሚ)ከሚያዝያ 15 እስከ ሚያዝያ 18/2018 ዓ.ም ለተከታታይ 4 ቀናት በሣይንስ ሙዚዬም የሚካሄደውን አህጉር አቀፍ የአዲስ አፍሪካ ሪል እስቴት ኤክስፖን የተመለከተ ጋዜጣዊ መግለጫ በዛሬው ዕለት በኢንተር ሌግዠሪ ሆቴል ተሰጠ፡፡
ኤክስፖው የኢትዮጵያ የሪል እስቴት አልሚዎች ማህበርና ዶክሳ ኢቨንትስ ጋር በጋራ የተዘጋጀ ነው፡፡
ከአምስት ሺህ በላይ የሚሆኑ ሰዎች እንደሚታደሙበት በሚጠበቀው በዚህ ኤክስፖ ላይ የሚመለከታቸው የመንግስት ተቋማት የስራ ኃላፊዎች፣ የፋይናንስ ተቋማትን ጨምሮ የአፍሪካ ሪል እስቴት ማህበር ዓባላት፣ የሪል እስቴት አልሚዎች፣ የኮንስትራክሽን ግብአት አቅራቢዎች፣ ኢንቨስተሮች እና የቤት ገዥ ማህበረሰብ ዓባላት ይሳተፉበታል፡፡
በዚህ ኤክስፖ ላይ ሦስት መርሃ-ግብሮች በአንድ ቦታ ላይ የሚካሄዱ ሲሆን የኢትዮጵያ ሪል እስቴት አልሚዎች ማህበር የተመሰረተበትን 1ኛ ዓመት ጠቅላላ ጉባኤ ያካሂዳል፤ በሁለተኛ ደረጃ ዓለም አቀፍ ኮንፈረንስ ይካሄድበታል፡፡ በሦስተኛ ደረጃ ኤግዚቪሽን ይካሄዳል፡፡ ይህም የሀገር ገጽታ ግንባታ እና ኮንፈረንስ ቱሪዝምን ለመሳብ የሚያገለግል ከመሆኑም በላይ አፍሪካውያን በዘርፉ ያላቸውን ተሞክሮ የሚለዋወጡበት መድረክ ስለሆነ ዲፕሎማሲያዊ ፋይዳው የጎላ እንደሆነ በማህበሩ የቦርድ ዓባላት ተገልጿል፡፡
በኤክስፖው ላይ የሪል እስቴት አልሚዎችና ቤት ገዥዎች በአንድ መድረክ ተገናኝተው መተማመንን የሚፈጥሩበት እና መረጃ የሚለዋወጡበት እንዲሁም ግዥና ሽያጭ የሚከናወንበት እንደሆነም ተገልጿል፡፡
ማህበሩ በተመሠረተበት የአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ የአምስት ዓመት ስትራቴጂውን ቀርጾ የጸደቀውን የሪል እስቴት አዋጅ ወደ መሬት ለማውረድ የሚያስችል ረቂቅ ደንብ ያዘጋጀ እንደሆነ ተገልጿል።
ማኅበሩ በተቋቋመበት በዚህ አጭር ጊዜ ውስጥ ከአንድ መቶ ያላነሱ ዓባላቱን በማሳተፍ በአጭር ጊዜ ውስጥ የሀገር ውስጥ አልሚዎች በውጭ ሀገራት ሄደው የሚሰሩበትን ዕድል ማመቻቸት፤ በቀጣይ 10 ዓመታት ዘላቂነትን የተከተለ ሁሉ-አቀፍ የቤት ልማት ማካሄድ እና በሚቀጥሉት 50 ዓመታት ዘላቂ የከተማ ልማት እንዲኖር የሚሰራ መሆኑ በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ ተነግሮአል ፡፡
በመጨረሻም ከተማና መሠረተ-ልማት ሚኒስቴር ለዘርፉ ዕድገትና ለማህበሩ መመስረት እንዲሁም ዘርፉ በህግ እንዲመራ ለማስቻል ላደረገው ጥረት አመስግነዋል፡፡