መጋቢት 6, 2026
አዲስ አበባ፣የካቲት 25 ቀን 2018 ዓ/ም (ከመልሚ)
የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር ከተለያዩ የመንግስት ተቋማት፣ የመንግስት የልማት ድርጅቶች፣ የግሉ ዘርፍ ተዋናዮች፣ ከባለድርሻ እና ከአጋር አካላት ጋር በመተባበር ‹‹ኢትዮጵያ ትገነባለች!›› በሚል መሪ ቃል ከሚያዚያ 9-12 ቀን 2018 ዓ/ም በአዲስ ኢንተርናሽናል ኮንቬንሽን ማዕከል የኢትዮጵያ የመሰረተ ልማትና የኮንስትራክሽን ሳምንት ለሚካሄደው መረሀ-ግብር በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ጋዜጣዊ መግለጫ ተሰጥቷል፡፡
ጋዜጣዊ መግለጫውን የሰጡት የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር ሚኒስትር ክብርት ወ/ሮ ጫልቱ ሳኒ የኢትዮጵያ የመሠረተ ልማትና የኮንስትራክሽን ሳምንት የሀገር ውስጥና አለም አቀፍ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ተዋናዎች፣ የፈጠራ ባለቤቶች የግንባታ ግብዓት አቅራቢዎች የሚሰባሰቡበት ሁሉን አቀፍ መድረክ በመሆኑ ዘርፉን በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚያሳድገው ገልጸዋል፡፡
የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ የሀገሪቷን ከፍተኛ ኢኮኖሚ የሚንቀሳቀስበት እና ለብዙሀኑ የስራ እድል የሚፈጥር ሲሆን ከሚያዚያ 9-12 ቀን 2018 ዓ/ም በአዲስ ኢንተርናሽናል ኮንቬንሽን ማዕክል የኢትዮጵያ የመሰረተ ልማትና የኮንስትራክሽን ሳምንት ፕሮግራም አስመልክቶ ከግንባታ እቃዎች እስከ ማሺነሪዎች እና ዲጂታል የግንባታ ቴክኖሎጂዎች ጨምሮ ዘላቂ መፍትሔዎች ሰፊ ምርቶችን እና አገልግሎቶች የሚቀርቡበት ፕሮግራም ነው ብለዋል፡፡
የኮንስትራክሽን የግንባታ ግብዓቶች በሀገር ውስጥ ምርት ለመተካት የሀገር ውስጥ ዘርፉ ተዋናዮች አዳዲስ ፈጠራዎች እና ልምዶች እንዲቀስሙ የቴክኖሎጂ እድገቶች እና የአሰራር ስርዓቶች እንዲገበዩ እንዲሁም ዓለም አቀፍ ኩባኒያዎች በፍጥነት በማደግ ላይ ያለውን የኢትዮጵያ የኮንስትራክሽን ገበያ ውስጥ የመግባት እድል እንዲያገኙ ምቹ ሁኔታን የሚፈጥር ይሆናል ብለዋል፡፡
ዘርፉ በማህበራዊ እና በኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ በገጠርም በከተማም ከፍተኛ አስተዋጽኦ የሚያበረክትና በመንግስት ደረጃ ከፍተኛ ሀብት የሚመደብለት የመሰረተ ልማት ተደራሽነት ለማረጋገጥ የተለያዩ አሰራሮችን በመከተል የዜጎች ፍትሐዊ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ እንደሆነም ተናግረዋል ክብርት ሚኒስትር፡፡