
ነሐሴ 1, 2025
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 22/2017 ዓ.ም፣ (ከመልሚ)
የከተማና መሠረተ-ልማት ሚኒስቴር እና የተጠሪ ተቋማት ከፍተኛ አመራሮችና በየደረጃው የሚገኙ የስራ ኃላፊዎች የተሳተፉበት የመንግስት አገልግሎትና አስተዳደር ሪፎርም ይፋዊ ማስጀመሪያ መርሃ-ግብር በዛሬው ዕለት በሚኒስቴር መ/ቤቱ አዳራሽ ተካሄደ፡፡
በሚኒስቴር መ/ቤቱ በተዋቀረ ዓብይ ኮሚቴና በሚ/ር መ/ቤቱና በተጠሪ ተቋማት በተሰየመ የቴክኒክ ኮሚቴ የተዘጋጀው የከተማና መሠረተ-ልማት ሚኒስቴር የመንግስት አገልግሎትና አስተዳደር ሪፎርም ፍኖተ ካርታ በክቡር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ የትምጌታ አስራት ቀርቦ በሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ኮሚሽነር፣ በክቡር መኩሪያ ኃይሌ (ዶ/ር) የቀረበውን የመንግስት አገልግሎትና አስተዳደር ፖሊሲ ገለጻ ተከትሎ ተጨማሪ ግብኣት ተሰጥቶበታል፡፡
እንደ ክቡር ሚኒስትር ዴኤታው ገለጻ በከተማና መሠረተ-ልማት ሚኒስቴር የተዘጋጀው የመንግስት አገልግሎትና አስተዳደር ሪፎርም ማስተግበሪያ ፍኖተ-ካርታ በ8 የትኩረት መስኮች ትኩረት አድርጎ የተዘጋጀ እንደሆነና የሪፎርሙ ዓላማም ለሀገራዊ ልማት ስኬት የሚያግዝ ግልጽ፣ ብቁና ገለልተኛ ሲቪል ሰርቪስ መገንባት ሲሆን የሪፎርሙ ዋና ግብም ግልጽ፣ ቀልጣፋ፣ ዘመናዊ እና ውጤታማ ተቋም በመፍጠር ዜጎችንና አገልግሎት ፈላጊዎችን በብቃት በማገልገል ምላሽ መስጠትና ማርካት መሆኑን በመግለጫቸው አብራርተዋል፡፡
በተመሳሳይ የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ኮሚሽነር፣ ክቡር መኩሪያ ኃይሌ (ዶ/ር) ቀርቦ የጋራ አስተሳሰብ ለመያዝ ያስቻለ ግንዛቤ የተፈጠረበት የመንግስት አገልግሎትና አስተዳደር ፖሊሲ ዓለም አቀፋዊና አህጉራዊ ሁኔታዎችንና የኢትዮጵያን ነባራዊ ሁኔታ በማገናዘብ የተዘጋጀ መሆኑን ገልጸው የፖሊሲው መዘጋጀት ዋነኛ ዓላማም ፈተና ላይ የወደቀውን የመንግስት አገልግሎትና መታከትና ዝለት የሚታይባቸውን ቀደም ሲል ስንጠቀምባቸው የነበሩ የለውጥ መሣሪያዎችን በአዲስ ሪፎርም በመተካት ዓለም ከደረሰበት የዕድገት ደረጃ ላይ ለመድረስ በመደበኛ የስራ ሰዓት ከሚከናወነው ተግባር ባሻገር ብሔራዊ አርበኝነትን የሚጠይቅ ተግባር ለመፈጸም ነጻና ገለልተኛ ሲቪል ሰርቫንት በመገንባት የሚፈለገውን ለውጥ ማምጣት አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ ነው ብለዋል፡፡
አያይዘውም ምንም እንኳ በንጉሱ ዘመን አንድ መቶ ሺህ የነበረው የሲቪል ሰርቫንት ቁጥር በአሁኑ ሰዓት በፌዴራልና በክልሎች ያለው የሰው ኃይል ሁለት ነጥብ አምስት ሚሊዮን የደረሰ ቢሆንም በዘመናዊ አሠራር የተደገፈ የአገልግሎት አሰጣጥ ጥራት እውን ሊሆን ባለመቻሉ ፖሊሲውን መቅረጽ የመንግስት አጀንዳ ሆኖ እንዲወጣ ያስገደደ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በሚኒስቴር መ/ቤቱ የተዘጋጀውን ፍኖተ ካርታ በተመለከተም ፈጥናችሁ ወደ ስራ መግባታችሁ ለለውጥ ያላችሁን ተነሳሽነት ያሳያል ካሉ በኋላ ወደ ሪፎርም ሳትገቡ የኮንስትራክሽን አገልግሎቶችን ወደ መሶብ አገልግሎት ማስገባታችሁ ፋና ወጊ ስራ እየሰራችሁ መሆኑን ያሳያልና ይሄንን ማስፋትና ማሳደግ ይጠበቅባችኋል ብለዋል፡፡
በመጨረሻም ፍኖተ-ካርታው በውስጡ ሊያካትታቸው የሚገቡ የቅርጽና የይዘት ዝርዝር ጉዳዮችን የተመለከቱ ምክረ-ሀሳቦችን በመስጠት ተቋማቸው አስፈላጊውን ድጋፍና እገዛ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ክብርት ሚኒስትር ወ/ሮ ጫልቱ ሳኒ በማጠቃለያ አስተያየታቸው ላይ እንደተናገሩት ቀድመን የጀመርናቸው ስራዎች ስላሉ የተሰጠንን ግብአት ተቀብለንና አሻሽለን የምንሰራ ይሆናል ካሉ በኋላ ለዘርፉ አመራሮችና የስራ ኃላፊዎችም ለለውጥ ያለንን ፍላጎት ራሳችንን ለለውጥ ዝግጁ በማድረግ በተሰጠን ኃላፊነት ልክ ለመስራት ራሳችንን ዝግጁ እናድርግ፤ እንበርታ! በማለት አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል፡፡
ሪፖርተር፡- ስለሺ ዘገዬ
የካሜራ ባለሙያ፡- አስመላሽ ተፈራ