መጋቢት 30, 2026

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 16/2018 ዓ.ም፣ (ከመልሚ)

የከተማና መሠረተ-ልማት ዘርፍ ማኔጅመንት ከ2019-2021 በጀት ዓመት በዘርፉ ለማከናወን በዕቅድ የተያዙ ፕሮግራሞችና ፕሮጀክቶችን ለማስተግበር በሚቻልበት ጉዳይ ላይ ተወያይቶ የበጀት ጥያቄው አዳዲስ ስራዎችን ታሳቢ ባደረገ መልኩ ተዘጋጅቶ ለገንዘብ ሚኒስቴር መላክ እንዳለበት ስምምነት ላይ ደረሰ፡፡

በስትራቴጂክ ጉዳዮች ስራ አስፈጻሚ በኩል ተዘጋጅቶ የቀረበው ዕቅድ በቀጣይ ሦስት ዓመታት በዘርፉ የሚሰሩ ሥራዎችን በተመለከተ በዋናው መ/ቤትና በተጠሪ ተቋማቱ የሚሰሩ ስራዎችን በዝርዝር የተመለከተ ሲሆን በዕቅድ የተያዙ ፕሮግራሞችና ፕሮጀክቶችን ለማስፈጸም ካለው ነባራዊ ሁኔታ ጋር ተያይዞ አዳዲስ ዕቅዶችንም ለማስፈጸም በሚያስችል ሁኔታ ተገቢው በጀት እንዲፈቀድ አሳማኝ ምክንያቶችን ይዞ መቅረብ እንደሚያስፈልግ አቅጣጫ ተቀምጧል፡፡

የቀጣይ ሦስት ዓመት (2019-2021) ዕቅዱ ሲዘጋጅ ከ2016-2018 በጀት ዓመት የተከናወኑ ዋና ዋና ተግባራትን አፈጻጸም የዳሰሰ ሲሆን የበጀት አጠቃቀምን፣ በተከናወኑ ሥራዎች ተገኙ ስኬቶችን እና በእጥረት የታዩ ጉዳዮችንም አመላክቷል፡፡ እንዲሁም የ2019 የፕሮግራም በጀት ዝግጅት ታሳቢዎችን፣ ፕሮግራሞች እና ፕሮጀክቶችን የቀጣይ ሦስት ዓመታት ዋና ዋና ተግባራትንም የዳሰሰ ነው፡፡

በውይይት መድረኩ ላይ ክብርት ሚኒስትር ወ/ሮ ጫልቱ ሳኒን ጨምሮ ክቡራን ሚኒስትር ዴኤታዎች፤ የተጠሪ ተቋማት ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች እና የሚኒስቴር መ/ቤቱ የማኔጅመንት አባላት ተሳትፈዋል፡፡

Posted in: ዜና