ታህሳስ 22, 2025
አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 6 ቀን 2018 ዓ/ም (ከመልሚ)
የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር ሙስናና ብልሹ አሰራሮችን በመከላከል ከሁሉም የፌደራል ተቋማት 3ኛ ደረጃ በመውጣቱ የዋንጫና የምስክር ወረቀት ሽልማት ተበረከቶለታል፡፡
ሽልማቱን የተረከቡት የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር ሚኒስትር ክብርት ወ/ሮ ጫልቱ ሳኒ እንደተናገሩት ተቋሙ ቀጣይነት ያለው አስራር ዘርግቶ መንግስት ያወረዳቸውን ሪፎርሞችን እውን በማደረግ ሁሉንም የከተማ አጀንዳዎች ከሙስናና ብልሹ አሠራሮች በጸዳ አኳኋን እስከታችኛው መዋቅር በማውረድ የከተማ ነዋሪው ፈጣን፣ግልጽነት የተሞላበትና ተጠያቂነት የሰፈነበት አገልግሎት መስጠት ይገባል ብለዋል፡፡
ክብርት ሚኒስትሯ አክለውም ዘርፍ ለሙስናና ለብልሹ አሰራር የተጋለጠ በመሆኑ በቀጣይነት ሁሉም አመራርና ሠራተኛ ከህሊናው ጋር የሚያስታርቅ፣ እራስን የሚያስከብር እና ለትውልድ የሚያሻገር ስራ በመስራት በከተሞች መልካም አስተዳደርን በማስፈን በቀጣይ ዓመት ከሦስተኛ ወደ አንደኛ ለመውጣት ከባለድርሻ አካላት ጋር በትብብርና በቅንጅት መስራት ይገባል ብለዋል፡፡
ሽልማቱ ለተቋሙ የተበረከተለት የሥነ ምግባር እና ጸረ-ሙስና ቀን በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ22ኛ ጊዜ እንደ ሀገር አቀፍ ደግሞ ለ21ኛ ጊዜ “ትውልድን በስነ- ምግባር ፤ ተቋምን በአሰራር ” በሚል መሪ ቃል የሀገሪቱ ም/ጠቅላይ ሚኒስቴር ክቡር አቶ ተመስገን ጥሩነህ እና የተለያዩ የሀገሪቱ ከፍተኛ የመንግስት ኃላፊዎች በተገኙበት ለሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የዋንጫና የምስክር ወረቀት ሽልማት እንደተበረከተለት ገልጸዋል፡፡
በዘንድሮው ዓመት 1ኛ የወጣው መከላከያ ሚኒስቴር ሲሆን 2ኛ የወጣው ደግሞ የገቢዎች ሚኒስተተር እንደሆኑ የተገለጸ ሲሆን ባለፈው በጀት ዓመት ከሁሉም ፌደራል ተቋማትሚኒስቴር መስሪ ቤታችን 2ኛ ወጥቶ እንደነበር በመድረኩ ታውቋል ፡፡
እንደዘርፍ የተቀናጀ የስነ-ምግባር ግንባታ እያካሄደ መገኘቱ፣ ተናባቢ የጸረ-ሙስና መከላከያ ዜዴዎችን እየተከተለ መስራት በመቻሉ ከተጠሪ ተቋማት ጋር ፎረም መስርቶ በመደገፍ፣ በመከታተል የፀረ-ሙስና ትግልን ተግባራዊ ማድረጉ፣ በፕሮጀክቶች ዙሪያ ብልሹ አሰራሮች እንዳይከሰቱ እና የማስተካከያ ርምጃዎችን በመተግበሩ እና መሰል አሰራርን በመከተሉ ሚኒስቴር መስሪያ ባቱን ተሸላሚ ማድረጉን ከስራ ክፍሉ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡