ታህሳስ 12, 2025

አዳማ፣ ህዳር 16፣ 2018 ዓ፣ም (ከመልሚ) በመረጃ አስተዳር ሥርዓት(MIS) ዙሪያ ለከተሞች ልማታዊ ሴፍትኔትና ስራ ፕሮጀክት ባለሙያዎች ተግባራዊ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ተሰጥቷል፡፡

ስልጠናው ፕሮጀክቱ በሚተገበርባቸው 12ቱ የኢትዮጵያ የክልል ከተሞች እና ሁለቱ የከተማ አስተዳደሮች በአጠቃላይ በ87 ከተሞች ፕሮጀክቱ ተግባራዊ በሚደረግባቸው፣ በ81 ከተሞች ደግሞ ክፍያ የሚፈጸምባቸው ሲሆን የክፍያ ጣቢያ በሚፈጸምባቸው 97 ከተሞች የመረጃ አስተዳደር ስርዓት ስልጠናው ከተሰጠ በኋላ ሲስተሙን ተግባራዊ እንደሚያደርጉ የከተሞች ልማታዊ ሴፍትኔትና ስራ ፕሮጀክት አስተባባሪ አቶ አንዱዓለም ገሠሠ ተናግረዋል ፡፡

የከተሞች ልማታዊ የምግብ ዋስትናና ሴፍትኔት መርሃ-ግብር ከገጠሪቱ የሀገሪቱ ክፍሎች በከፍተኛ ደረጃ እየጎረፉ የሚገኙ አካል ጉዳተኞችን፣ ሀገራቸውን በተለያዩ ሙያዎች ያገለገሉ ረዳት የሌላቸው የዕድሜ ባለጸጋዎች በዘላቂነት በየወሩ ቀጥተኛ ድጋፍ በመስጠት መሆኑን የገለጹት አቶ አንዱዓለም ሠርተው መለወጥ የሚችሉ ወጣቶችን ደግሞ በተለያዩ የከተማ ልማቶች ተደራጅተው በመሥራት ለተከታታይ ሶስት ዓመታት ድጋፍ ከተደረገላቸው በኋላ ቋሚ በሆነ የሥራ መስክ ተሠማርተው እንዲሠሩ በማስቻል ነው ሲሉ የፕሮጀክቱ አስተባባሪ ተናግረዋል፡፡

በግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠናው የተሳተፉት በኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ስር የሚገኙ የበደሌ ከተማና የሸገር ከተማ ፋይናንስ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች፣ ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ባለሙያዎች፣ የመረጃ ባለሙዎች፣ የፕሮጀክት አስተባባሪዎች እና የፋናንስ ስፔሻሊስቶች እንደተሳተፉ የከተሞች ልማታዊ ሴፍትኔትና ስራ ፕሮጀክት የኢንፎርሜሽን ሲስተም እና ማኔጅመንት ስፔሻሊስት አቶ ይታወስ አደላ ገልጸዋል ፡፡

የስልጠናው ዋና ዓላማ በከተሞች የሴፍትኔት ተጠቃሚዎች ማንኛውም ወርሃዊ ክፍያዎች ሲፈጸሙ ወቅቱን የጠበቀ፣ ጥራቱ የተረጋገጠ፣ ደህንነቱ የተጠበቀ፣ የተጠቃሚዎች መረጃ ቀጣይነት እና ወጥነት ባለው መንገድ መረጃዎችን ይዞ ከባንክ ጋር ክፍያዎች ሲፈጸሙ ግልጽነት የተሞላባቸው የመረጃ አስተዳር ሥርዓት (MIS) በመዘርጋት ዘመናዊ የድጅታል አሠራርን ተግባራዊ እያደረጉ ልማዳዊ አሠራርን አስቀርቶ ማንኛውንም ዳታ በአስተማማኝ መንገድ መያዝ እንደሚያስችል አቶ ይታወስ ተናግረዋል፡፡

ስልጠናው በተግባር ታግዞ ለተከታታይ ሦስት ቀናት እንደሚሠጥ በመርሃ-ግብሩ ተመልክቷል፡፡

Posted in: ዜና