ታህሳስ 22, 2025

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 7/2018 ዓ.ም፣ (ከመልሚ)

በከተማና መሠረተ-ልማት ሚኒስቴርና በትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር በጋራ የተዘጋጀ ረቂቅ የመንገድና ትራንስፖርት ፖሊሲ በባለድርሻ አካላት ተገምግሞ ፖሊሲውን ለማዳበር የሚያስችሉ ግብኣቶች ተሰባስበውበታል፡፡

በግምገማ መድረኩ ላይ የሁለቱም ሚኒስቴር መ/ቤቶች ክቡራን ሚኒስትሮችና ሚኒስትር ዴኤታዎች፣ እንዲሁም የዘርፉ ተጠሪ ተቋማት ኃላፊዎች፣ ባለድርሻ አካላት እና ጥሪ የተደረገላቸው ዕንግዶች ተሳትፈውበታል።

በመርሃ ግብሩ ላይ ስለ ፖሊሲው አስፈላጊነት ተገልፆ የረቂቅ ፖሊሲው ሠነድ በሁለቱም ሚ/ር መ/ቤቶች በኩል የቀረበ ሲሆን በቀረቡት ሠነዶች ላይ የጋራ ውይይት ተደርጎ ከተወያዮቹ ፖሊሲውን ለማዳበር የሚያስችሉ ግብአቶች ተሰባስበውበታል፡፡

በፖሊሲው አስፈላጊነት ላይ እንደተገለጸው ቀደም ሲል በሁለቱ ተቋማት በተናጠል ሊሰራ ታስቦ የነበረው የተናጠል የፖሊሲ ጥናት የሁለቱም ተቋማት ስራ እርስ በርስ የሚደጋገፍ እንጂ የማይነጣጠሉና ከራሳቸው አልፎ የሌሎችንም ተቋማት ቅንጅት የሚጠይቅ በመሆኑ አቅምን አቀናጅቶ ለመጠቀም፣ ቅንጅትን ለመፍጠር፣ ስራዎችን በቴክኖሎጂ በማስተሳሰር ደህንነቱ የተረጋገጠ፣ ዘመናዊና ዘላቂ የመንገድና የትራንስፖርት አገልግሎት በመስጠት ፍትሃዊ የመንገድና የትራንስፖርት ተደራሽነትን ለማስፋት ፖሊሲው አንድ ሆኖ በጋራ መውጣቱ አስፈላጊ መሆኑ ተገልጿል።
የተቀናጀ፣ ደህንነቱ የተረጋገጠ፣ አካታችና ዘላቂነት ያለው፣ በሥርዓት የሚመራ ዘመናዊና ዘላቂ የመንገድ ትራንስፖርት አገልግሎት ለመስጠት የፖሊሲው መውጣትና ጸድቆ ወደስራ መግባት እያደገና እየዘመነ ከሚሄደው የህብረተሰብ ፍላጎት እና ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ዕድገት ጋር አብሮ ተሳስሮ የሚጓዝ እንዲሆን ለማድረግ ያስችላልም ተብሏል፡፡

በውይይቱ ሂደትም ረቂቅ ፖሊሲው የመንገድ ደህንነትን፣ የአሽከርካሪዎች ብቃትን፣ የትራፊክ ማኔጅመንትን፣ ከአየር ንብረት ጋር የሚስማማ መሆንን ታሳቢ ያደረገ መሆኑን በማንሳት ሊሻሻሉ በሚገባቸው ጉዳዮች ላይ ተጨማሪ ግብአቶች ከቤቱ ተነስተዋል።

በመጨረሻም የከተማና መሠረተ-ልማት ሚኒስትር ክብርት ወ/ሮ ጫልቱ ሳኒ እና የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ክቡር ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር) በሰጡት የማጠቃለያ አስተያየት ዘርፉ ለሀገሪቱ ማበርከት የሚጠበቅበትን ውጤት እንዲያስገኝ ጠንካራ የመንግስትና የግል አጋርነት ሊኖር እንደሚገባና አካባቢያዊና ተፈጥሯዊ ሥነ-ምህዳርን የጠበቀ፤ ቀጠናዊ ትስስርን የሚያጠናክር እንዲሆን በማድረግ እክል አልባ የትራንስፖርት እንቅስቃሴ እውን እንዲሆን ምቹ፣ ደህንነቱ የተረጋገጠ አካታች ፖሊሲ እንዲሆን መስራት እንደሚያስፈልግ ተገልጿል፡፡

Posted in: ዜና