
ሰኔ 24, 2025
አዳማ፣ሰኔ 13 ቀን 2017 ዓ/ም (ከመልሚ)
በከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር፣ በቤቶች ልማት መሪ ስራ አስፈጻሚ አዘጋጅነት በመኖሪያ ቤት ኪራይ ቁጥጥርና አስተዳደር አዋጅ ቁጥር 1320/2016 እና በሪል እስቴትና በቋሚ ንብረት ግመታ አዋጅ ቁጥር 1357/2017 ላይ ትኩረቱን ያደረገ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ከሲዳማ፣ ከማዕከላዊ ኢትዮጵያ፣ ከደቡብ ኢትዮጵያ እና ከደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ለተውጣጡ በክልል፣ በዞን እና በከተማ ደረጃ ለሚገኙ በቤቶች ልማት ዘርፍ ላሉ የዘርፉ አመራሮች እና ባለሙያዎች የአቅም ግንባታ ስልጠና በአዳማ ከተማ ተሰጠ፡፡
መድረኩን በይፋ ያስጀመሩት የቤቶች ልማት መሪ ስራ አስፈጻሚ፣ ወ/ሪት ትዕግስት ዓለሙ በመክፈቻ ንግግራቸው እንዳሉት ከተሞች የአንድ ማህበረሰብ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ማዕከላት መሆናቸውን ገልጸው በቤት ልማት ዙሪያ ቀደም ሲል የቤት አቅርቦት ችግርን ለመፍታት መንግስት ቤቶችን በራሱ አቅም ገንብቶ ለቤት ፈላጊዎች ለማስተላለፍ ያደርግ የነበረው ጥረት የሚፈለገውን ውጤት ሊያመጣ ባለመቻሉ የፖሊሲ ለውጥ በማድረግ 20 በመቶ የሚሆኑ ቤቶች በመንግስት፤ 80 በመቶ የሚሆኑት ቤቶች ደግሞ በተለያዩ የቤት ልማት አማራጮች በግሉ ዘርፍ ተሳትፎ እንዲለሙ በመደረጉ ውጤታማነታቸው መረጋገጡን ገልጸዋል፡፡
ከዚሁ ጋር በማያያዝ የመድረኩን መዘጋጀት ዓላማ አስመልክተው እንደተናገሩት መንግስት የህዝብ አጋርነቱን ለማሳየት የቤት ልማቱንና ቤቶችን በስርዓት ለማስተዳደር ያወጣቸውን አዋጆች አፈጻጸም ከዘርፉ የ10 ዓመት መሪ ዕቅድ ጋር በማነጻጸር ከተቀመጠው ግብ አንጻር ክልሎች በምን ያህል ደረጃ አዋጆችን እንደፈጸሟቸው ገምግሞ በቀሪዎቹ የዕቅዱ አመታት ያሉትን ክፍተቶች ለይቶ በመሙላት ተፈጻሚ እንዲሆኑ ማድረግን ያለመ ነው ብለዋል፡፡
በመድረኩ ላይ በመሪ ስራ አስፈጻሚው የዴስክ ኃላፊዎች በአቶ ታፈሰ ነጋ እና በአቶ በላይ ካህሳይ አቅራቢነት የቤት ልማት መሪ ዕቅድና ስትራቴጂ፤ በሪል ስቴት ዙሪያ የተደረገ ጥናትና ደንብ፤ እንዲሁም በመኖሪያ ቤት ኪራይ ቁጥጥር እና አስተዳደር አዋጅ ላይ ያተኮሩ ሰነዶች ቀርበው የወጡትን የህግ ማዕቀፎች ለማስፈጸም በአራቱ ክልሎች የተሰሩ ስራዎችና ክልሎች የሚገኙበትን ነባራዊ ሁኔታ የተመለከተ ሪፖርት ቀርቧል፡፡
የቀረቡትን ሰነዶች መነሻ በማድረግ በተደረገው የጋራ ውይይት የኪራይ ቤቶችን፣ በግሉ ዘርፍ የሚለሙ ቤቶችን፣ የገጠር ማዕከላትን፣ የማህበር ቤቶችን እና ሪል እስቴቶችን እንዲሁም የቤቶችን መረጃ በተዘጋጀው ሶፍትዌር ለማስገባት በተሰሩ ስራዎች ላይ ክልሎች ያሉበትን ደረጃና በስራ ሂደት የገጠሟቸውን ችግሮች ለመፍታት የሄዱበትን ርቀት የገለጹ ሲሆን በተዘጋጀው መድረክ ግንዛቤያቸው ማደጉንና የፌዴራል መ/ቤቱ ቀጣይ ድጋፍ እንዳይለያቸው ገልጸዋል፡፡
በመድረኩ ማጠቃለያ ላይ በተሰጡ ቀጣይ አቅጣጫዎች ከ2013-2022 ዓ.ም በዘርፉ ከተያዘው የ10 ዓመቱ መሪ የልማት ዕቅድ አኳያ አፈጻጸሙ የዕቅድ ዘመኑን አጋማሽ ውጤት የሚያሳይ ባለመሆኑ በቀሪው ዘመን ዕቅዱን ለማሳካት በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ እና ይሄም የአመራሩን ቁርጠኝነትና የአመራሩንና የፈጻሚውን የተናበበ እና የተቀናጀ አሠራር የሚጠይቅ ስለሆነ ለተፈጻሚነቱ የጋራ ርብርብ ማድረግ እንደሚገባ አቅጣጫ ተቀምጧል፡፡
ሪፖርተር፡- ስለሺ ዘገዬ
የካሜራ ባለሙያ፡- ፈዬ ደሜ