ነሐሴ 28, 2025

ድሬዳዋ ፤ ነሐሴ 13/2017(ከመልሚ)፡-
በብልፅግና ዘመን ድንጋይ አስቀምጦ መጥፋት፣ ጀምሮ መተው፣ ከጥራት በታች ሠርቶ መመረቅ አይፈቀድም” ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ተናገሩ ።
ክቡር ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ 144 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለውን የሚኤሶ – ድሬዳዋ የፍጥነት መንገድ ግንባታን አስጀምረዋል።

በማስጀመሪያ መርኃግብሩ ላይ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊና የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አደም ፋራህ፣ የሶማሌ ክልል ር/መስተዳድር ክቡር አቶ ሙስጠፌ ሙሀመድ የኢፌዴሪ ከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር ሚኒስትር ክብርት ጫልቱ ሳኒ፣ ጨምሮ ፌደራልና የክልል መንግሥታት ከፍተኛ የአመራሮቹ ተገኝተዋል።

መንገድ ለሀገር ውስጥ ምርቶች ታላላቅ የገበያ ዕድሎችን የሚፈጥርና ቀጣናዊ የነጻ የንግድ ግቦችን ከማሳካት አኳያ ትልቅ ድርሻ አለው ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደ ኢትዮጵያ በማደግ ላይ ላለ ሀገር፣ የኢኮኖሚ ዕድገትን ለማጎልበትና የዜጎችን የኑሮ ደረጃ ለማሻሻል የመንገድ መሠረተ ልማት ላይ ኢንቨስት ማድረግ እጅግ አስፈላጊ መሆኑንም ተናግረዋል።

የምሥራቁ ኮሪደር የሀገራችን የገቢ እና ወጪ ንግዶች የሚሳለጡበት ትልቁ የንግድ መሥመር መሆኑን ጠቅሰው፤ ከወደብ ወደ ማዕከላዊ የሀገሪቱ ክፍል የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ወጪና ጊዜ ቆጣቢ እንዲሆኑ እንደሚያስችልም ተናግረዋል።

የሚኤሶ -ድሬዳዋ የፍጥነት መንገድ መንግስት ትራንስፖርትን ለማዘመን ያለውን ቁርጠኝነትና የበለጸገች ኢትዮጵያን የመገንባት ራዕያችን እውን እየሆነ መምጣቱን የሚያሳይ ወሳኝ መሠረተ ልማት መሆኑን በማብራራት።

ይህ ግዙፍ የኢኮኖሚ አውታር የሆነው የሚኤሶ – ድሬዳዋ የፍጥነት መንገድ በታቀደለት ደረጃና ጊዜ እንዲጠናቀቅ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ኃላፊነታቸውን በብቃት እንዲወጡ አሳስበዋል ክቡር ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ።

የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስትር ክብርት ወ/ሮ ጫልቱ ሳኒ በበኩላቸው የፍጥነት መንገዱ ሁለት ክልሎችንና የድሬዳዋ ከተማን በማስተሳሰር ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ መስተጋብሮችን በከፍተኛ ደረጃ እንደሚያጎለብት ተናግረዋል።

ፕሮጀክቱ ኢትዮጵያ የምትገኝበት የአፍሪካ ቀንድ ትስስር ኢኒሼቲቭ አካል ሲሆን ኢትዮጵያ ሀገራችን ከቀጠናው ሀገራት ጋር ለምታደርገው የንግድና የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት የላቀ ፋይዳ ያለው፣ የትራንስፖርት ወጪንና የትራፊክ አደጋን የሚቀንስ መሆኑንም ተናግረዋል።

ፕሮጀክቱ የህልማችን ነፀብራቅ፣ የመሻት ማሳያ፣ የአገር ፍቅርና ትጋት ውጤት ነው ያሉት ሚኒስትሯ፤ ዘመናዊ፣ደህንነቱ የተጠበቀና ምቹ ትራንስፖርት ለመስጠት የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል።

ፕሮጀክቱ በሁለት ምዕራፍ ተከፍሎ የሚገነባና 144 ኪሎ-ሜትር የሚሸፍን ሲሆን ከአለም ባንክ በተገኘ 62 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር የሚገነባ እና የቻይና ሲቪል ኢንጂነሪንግ ኮንስትራክሽን ኮርፖሬሽንና ሲችዋን ሮድ ኤንድ ብሪጅ በጥምረት እንደሚያከናውኑት እና በአራት አመት ውስጥ ይጠናቀቃል ተብሎ እንደሚጠበቅም ክብርት ሚኒስትር ተናግረዋል።

Posted in: ዜና