ጥር 22, 2026
አዲስ አበባ፣ ጥር 8 ቀን፣ 2018 ዓ.ም (ከ.መ.ል.ሚ) በቱሉ አራራ ከተማ የተቀናጀ ሞዴል መንደር ግንባታ ስኬት በላቀ ደረጃ ለተሳተፉ ባለድርሻ አካላት የምስጋና እና የዕውቅና መርሃ-ግብር ተካሄዷል ፡፡
የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር በክረምት በጎፈቃድ አገልግሎት መርሃ-ግብር ያስገነባቸውን የተቀናጀ ሞዴል መንደር ታህሳስ 29 ቀን 2018 ዓ.ም በክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ (ዶ/ር) በይፋ ተመርቀው ለተጠቃሚዎች መተላለፋቸው ይታወቃል፡፡
ዘመናዊ የተቀናጀ ሞዴል መንደር ገንብቶ ለተጠቃሚዎች ማስረከብ የተቻለው ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት እና በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ስር ከሚገኙ የተጠሪ ተቋማት ጋር በመተባበር 150 ዜጎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ እንደሆነ በይፋ አስመርቆ ለተጠቃሚዎች ማስተላለፉን ተከትሎ በግንባታው ሂደትና ስኬት ከፍተኛ ሚና ለነበራቸው አካላት የዕውቅና እና የምስጋና ምስክር ወረቀት መስጠት ማስፈለጉን ክብርት ሚኒስትር ወ/ሮ ጫልቱ ሳኒ ተናግረዋል፡፡
በሌላ በኩል የምስጋና የምስክር ወረቀት የተበረከተላቸው በሀገሪቱ በኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው ተሰማርተው ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በተለያዩ በጎ አድራጎት ስራዎች እንዲተባበሩ ጥሪ ስያደርግላቸው ላለፉት በርካታ ዓመታት ከፍተኛ አስተዋጾኦ ሲያደርጉ የቆዩና አሁንም በቱሉ አራራ ከተማ የተቀናጀ ሞዴል መንደር ግንባታ ስኬት በላቀ ደረጃ በሙያቸው፣ በእውቀታቸው እና በገንዘባቸው የዜግነት እና ማህበራዊ ኃላፊነታቸውን ለተወጡ አካላት በከተማና መሠረተ-ልማት ሚኒስቴር ሚኒስትር ክብርት ወ/ሮ ጫልቱ ሳኒ ምስጋና ተችሯቸዋል፡፡
በዚህ መርሃ-ግብር የተሳተፉ ድርጅቶችና ግለሰቦች የዜግነት አገልግሎታችሁን እንደባለፈው ሁሉ በሀገር ደረጃ ሞዴል ሊሆኑ የሚችሉ ሁሉም መሠረተ-ልማት የተሟላላቸውን መኖሪ መንደሮችን ለመገንባት በምናደረገው ጥረት እና ቀሪ ስራዎችን በጋራ ለመስራት ከጎናቸው እንዲሰለፉ ክብርት ሚኒስትሯ ጥር አቅርበዋል ፡፡
የተቀናጀ ሞዴል መንደር ለተጠቃሚዎች የተላለፉት በኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሰት በደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን፣ ሰበታ ሀዋስ ወረዳ፣ በቱሉ አራራ ከተማ መሆኑን ክብርት ሚኒስትሯ ገልጸው ሞዴል መንደሩ ለዜጎች ምቹ፣ ጽዱ፣ ለኑሮ ተስማሚ፣ የውስጥ ለውስጥ መንገድ የተሟላላቸው፣ በኤሌክትሪክና በፀሀይ ኃይል የሚጠቀሙ፣ የስፖርት ማዘውተሪያ የተሟላላቸው፣ የነዋሪዎችን የኑሮ ደረጃ በዘላቂነት ለማሻሻል የከተማ ግብርናን የሚጠቀሙ፣ የምርትና የገበያ ሰንሰለትን ያካተተ የተቀናጀ አሰራር እንደተዘረጋላቸው በዕውቅና መድረኩ ላይ ተናግረዋል ፡፡