ጥር 15, 2026

አዲስ አበባ፣ታህሳስ 24/2018፣ (ከመልሚ)

የገጠር ትስስርና ተደራሽነት ለምግብ ዋስትና ፕሮግራም ከዓለም ባንክ በተገኘ ድጋፍ እና በፌዴራልና በክልል መንግስታት መዋጮ በከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር አስተባባሪነት ከ2017 በጀት ዓመት ጀምሮ በሁሉም ክልሎችና በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር የአዳዲስ የገጠር መንገድ ግንባታ፣ የጥገና መንገድ ግንባታ፣ የተንጠልጣይ ድልድይ ግንባታ እና የልዩ ልዩ የመሻገሪያ ድልድይ ግንባታ በማከናወን ላይ ይገኛል፡፡

በመሆኑም የክልሎችን አቅም ማጠናከርና ፕሮግራሙ መሬት ላይ እንዲወርድ በፕሮግራሙ የአቅም ግንባታ በአይፒኤፍ (IPF Window) በዕቅድ ተይዞ በሚኒስቴር መ/ቤቱ በኩል የተገዙ 28 የነዳጅ ተሸከርካሪዎችና 130 ሞተር ብስክሌቶች ርክክብ በዛሬው ዕለት የተደረገ ሲሆን በግዢ ሂደት ላይ የሚገኙ ተጨማሪ 88 የግንባታ ማሽነሪዎችና 145 የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ መገልገያዎች በቀጣይነት የሚሰጡ ይሆናል፡፡

በርክክብ ሥነ-ስርዓቱ ላይ የተገኙት ክብርት ሚኒስትር ወ/ሮ ጫልቱ ሳኒ እንዳሉት የተገኘው ድጋፍ በ5 ዓመት እንዲከናወን ዕቅድ የተያዘ ቢሆንም መንግስት ካለው የልማት ፍላጎት አንጻር የህዝቡን የልማት ጥያቄ ለመመለስ በ3 ዓመት ጊዜ ውስጥ አጠናቆ ወደ ሌሎች ቀጣይ ፕሮጀክቶች ለመግባት ባለው ቁርጠኛ አቋም መሠረት ፈጠራና ፍጥነት በታከለበት ሁኔታ የተያዘውን ዕቅድ ማሳካት ይጠበቅብናል ብለዋል፡፡

አያይዘውም የተሰጡት የሞተር ብስክሌት እና የነዳጅ ተሸከርካሪዎች ለታለመላቸው ዓላማ ብቻ መዋል እንዳለባቸውና ሚኒስቴር መ/ቤቱም ክትትልና ቁጥጥር እንደሚያደርግ ገልጸዋል፡፡ የተደረጉት ድጋፎች በመንግስት የበጀት ቀመር መሠረት ፕሮግራሙ በሚፈጸምባቸው 126 ወረዳዎች ላሉ ፕሮጀክቶች ነው፡፡

ክልሎችም በበኩላቸው በመደመር መንግስት እሳቤ የተሰጣቸውን አደራ ተቀብለው በተባለው የ3 ዓመት ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅና ተጨማሪ ሀብት ፈጥረው ለሌላ አዲስ ፕሮግራም እንደሚዘጋጁ ቁርጠኛ መሆናቸውንና ከቃል ባለፈ በተግባር ለማረጋገጥ ቃል ገብተዋል፡፡

በርክክብ ሥነ-ስርዓቱ ላይ ሚኒስትሮች፣ የዓለም ባንክ ተወካዮች እና የክልሎች የመንገድ ልማትና ትራንስፖርት ቢሮ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል፡፡

Posted in: ዜና