ጥር 1, 2026

በገጠር ትራንስፎርሜሽን ማዕቀፍ የገጠር ቤትና መሠረተ-ልማት የንቅናቄ መድረክ
በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል፣ በሃድያ ዞን፣ ሆሳዕና ከተማ መካሄድ ጀመረ፡፡

በንቅናቄ መድረኩ ላይ በሚኒስቴር መ/ቤቱ በየደረጃው ያሉ አመራሮች፤ የተጠሪ ተቋማት የስራ ኃላፊዎች፤ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ምክትል ርዕሰ-መስተዳድርን ጨምሮ የክልል የከተማ ልማትና የመንገድ ዘርፍ ቢሮ ኃላፊዎች፣ የዞን አስተዳዳሪዎች፣ የዩኒቨርሲቲ ማህበረሰብ ዓባላትና የተቋማት የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል፡፡

መድረኩን በይፋ ያስጀመሩት የከተማና መሠረተ-ልማት ሚኒስቴር ሚኒስትር ክብርት ወ/ሮ ጫልቱ ሳኒ በመክፈቻ ንግግራቸው ቤት ለሰው ልጅ መሠረታዊ ፍላጎት ከሆኑት መካከል አንዱ እንደሆነና ሀገራችን ኢትዮጵያ በፈረመቻቸው ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ድንጋጌዎች ውስጥ የተካተተ መሆኑን አስታውሰው ቤት ከመኖሪያነት ባለፈ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ፋይዳው የጎላ እንደመሆኑ መጠን በገጠር የሚኖረው 76 በመቶ የሚሆነው ህዝባችን ኑሮው እንዲሻሻል ገጠሩን ከከተማ ጋር በመንገድ መሠረተ-ልማት በማስተሳሰር የተሟላና ለኑሮ ምቹ በሆነ አካባቢ ኑሮውን እንዲመራ ለማድረግ መንግስት በትኩረት እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የመድረኩን መዘጋጀት ዓላማም ሲገልጹ በኢትዮጵያ የገጠር ትስስርና ተደራሽነትን በማስፋት ረገድ የሚደረገውን የመንገድ ግንባታ ከገጠር ማዕከላት የመኖሪያ ቤት አቅርቦት ጋር በማስተሳሰርና ቅንጅታዊ አሠራርን በማጎልበት በዘርፉ የተሰማሩ አመራሮችና ባለሙያዎች የአቅም ግንባታ እንዲያገኙና የልምድ ልውውጥ እንዲያኙ በማድረግና ሰፊ ንቅናቄ በመፍጠር የተቀናጀና ዘላቂ የገጠር ትራንስፎርሜሽንን ለማፋጠን በቅንጅት፣ በፍጥነት እና ፈጠራ በተሞላበት ሁኔታ ቀን ከሌት በመስራት የገጠሩን ማህበረሰብ ህይወት ወደ ተሻለ ደረጃ ለማሸጋገር እንደሆነ በመግለጽ ከግብርና ትራንስፎርሜሽን ወደ ገጠር ትራንስፎርሜሽን፤ ከገጠር ትራንስፎርሜሽን ወደ መዋቅራዊ ትራንስፎርሜሽን የሚደረገው ሽግግር በተቀናጀ አግባብ ሊሳለጥ እንደሚገባው ተነግረዋል፡፡

የገጠር ቤት ጉዳይን በአግባቡ የተመለከተ አጠቃላይ የቤት ፖሊሲም በመጠናቀቅ ላይ መሆኑን አስታውሰዋል፡፡

የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት ያስተላለፉት፤ በም/ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የከተማና መሠረተ-ልማት ቢሮ ኃላፊው ክቡር አቶ ስንታየሁ ወ/ሚካኤል በበኩላቸው የመድረኩን አስፈላጊነት ሲገልጹ፡- የእርስ በርስ ልምድ በመለዋወጥ አቅማችንን የምናጎለብትበት፣ ግልጽ የማስፈጸም ተልዕኮ የምንወስድበት እና የህብረተሰባችንን የኑሮ ሁኔታ የምንለውጥበት መድረክ ነው ብለዋል፡፡

በንቅናቄ መድረኩ ላይ የገጠር ቤት ልማት ከየት ተነስቶ የት ደረጃ ላይ እንደደረሰ የሚያሳይ ገለጻ፣ የተሻሻለ የገጠር ቤት አሰራር፤ የአማራ ክልል የገጠር ቤት ተሞክሮ፣ በማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በክቡር ጠ/ሚ/ር ኢኒሼቲብ የተሰሩ የአርሶ አደር ሞዴል መንደር ግንባታ ተሞክሮ የቀረበ ሲሆን ከአካባቢ ሥነ-ምህዳር ጋር የተጣጣሙ የባዮ ኢንዛይም የግንባታ ቴክኖሎጂዎች ጥናት፣ የገጠር መንገድ ትስስር ለምግብ ዋስትና ከገጠር ማዕከላት የቤት ልማት ጋር ያለው ቁርኝትና የቅንጅት አቅጣጫን የተመለከተ ገለጻ በዩኒቨርሲቲዎች፣ በክልሎችና በሚኒስቴር መ/ቤቱ አመራሮች ቀርቦ ውይይት የተደረገ ሲሆን የፓናል ውይይትና የጋራ ውይይት መድረክ ተካሄዷል፡፡

በመጨረሻም ክብርት ሚኒስትር ወ/ሮ ጫልቱ ሳኒ በሰጡት የማጠቃለያ አስተያየት ትኩረት ከሰጡባቸው ጉዳዮች መካከል የገጠር ማዕከላት፣ የመሬት አጠቃቀም ፕላን (ስኬች ፕላን) ሊኖራቸው እንደሚገባ፤ የጉባ ብስራቶች ተብለው በክቡር ጠ/ሚ/ር ዐብይ አህመድ (ዶ/ር) ይፋ የተደረጉ የቤት ልማት ፕሮግራሞች ዕውን እንዲሆኑ መስራት እንደሚገባ፤ ሀገር በቀል ልምዶችንና ዕውቀቶችን በማስፋት የገጠር ማዕከላትን መገንባት እንደሚያስፈልግ፤ የአንድ ማዕከል አገልግሎት መስጫን ማጠናከር እንደሚገባ እና የመንግስት አገልግሎትና አስተዳደር ሪፎርምን አጥንተን በሁለተኛው ዙር ለመግባት ጥረት እያደረግን ስለሆነ አገልግሎትን ማዘመን የሁሉም ተቋማት ግዴታ እንደሆነ አቅጣጫዎችን አስቀምጠዋል፡፡

Posted in: ዜና