ጥር 1, 2026
ሆሳዕና፣ታህሳስ 22/2018 ዓ.ም፣ (ከመልሚ)
በገጠር ትራንስፎርሜሽን ማዕቀፍ የገጠር ቤትና መሠረተ-ልማት የንቅናቄ መድረክ በአዳራሽ ከተደረጉ ውይይቶች ባሻገር በሆሳዕና ከተማ የተገነቡ የኮሪደር ልማት ስራዎችና ሌሎች ፕሮጀክቶች ጉብኝት የተደረገ ሲሆን በሁለተኛው ቀን ውሎም በክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ (ዶ/ር) ሀሳብ አፍላቂነት በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል፣ በሃዲያ ዞን፣ ሊሞ ወረዳ፣ ዲባንጮ የገጠር ቀበሌ ማዕከል የተገነቡ የአርሶ አደር ሞዴል የመኖሪያ መንደሮች ጉብኝት ተካሄዷል፡፡
በሆሣዕና ከተማ የተገነቡ የኮሪደር ልማትና ሌሎች ፕሮጀክቶች ለጎብኝዎች ግርምትን የፈጠሩ ናቸው፡፡ ክልሉ ከተቋቋመ ሁለት ዓመት ተኩል በሆነ አጭር ጊዜ ውስጥ እራሱን አደራጅቶ ይህን ሁሉ ለውጥ ማምጣት መቻሉ ለጎብኝዎች ከአዕምሮ በላይ እንደሆነባቸው ከጉብኝቱ መረዳት ይቻላል፡፡ ክልሉ የዘንድሮውን የብሔር፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ቀን በዓል የመዝጊያ ሥነ-ስርዓት ማክበር የቻለውም የህን አቅም በመፍጠሩ ነው፡፡
ሞዴል መንደሮቹ የተለያዩ የጓሮ አትክልትና ፍራፍሬዎች፣የንብ ማነብ፣ የዶሮ ዕርባታ፣ የወተት ላሞች ዕርባታን ያካተቱ፤ አንድ በከተማ ውስጥ የተሻለ ህይወት የሚመራ ቤተሰብ የሚኖረው ዓይነት ህይወት የተሟላላቸው ናቸው፡፡ ባለ ሦስት መኝታ ቤት የሆኑ፣ ሳሎንና ኪችን የተሟላላቸው ሲሆኑ መታጠቢያ ቤትና መጸዳጃ ቤትም አላቸው፡፡ የተሟላ የ24 ሰዓት አገልግሎት የሚሰጥ በባዮጋዝ የሚሰራ የኤሌክትሪክ አገልግሎት የሚያገኙም ናቸው፡፡ ዘመናዊነትን የተከተለ የአኗኗር ዘይቤ አላቸው፡፡ ለቤቱ የሚያስፈልጉ ቁሳቁሶች የተሟሉላቸው የመኖሪያ መንደሮች ናቸው፡፡ ይህን ተከትሎ በቀጣይ በአንድ ወረዳ አንድ የገጠር ማዕከልን ዕውን የማድረግ ዕቅድ እንዳላቸውም አመራሮች ገልጸዋል፡፡
በጉብኝቱ የተሳተፉ ከሀገሪቱ ክልሎች፣ ዞኖችና የከተማ አስተዳደሮች የተውጣጡ ጎብኝዎችም ባዩት ነገር ከመደነቅ ባለፈ ትልቅ መነሳሳትን እንደፈጠረላቸው በመግለጽ ያገኙትን ልምድና ተሞክሮ ወደ ተግባር ለመቀየር ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ የጉብኝቱ ዓላማም ይሄው ስለነበር መድረኩና ጉብኝቱ ዓላማውን ሙሉ በሙሉ ያሳካ ነበር፡፡