ጥቅምት 10, 2025

አድስ አበባ፣ መስከረም 9 ቀን 2018 ዓ.ም (ከመልሚ) በ10ኛው የኢትዮጵያ ከተሞች ፎረም ከተሞች ከአስር አመቱ ከታቀዱ ያለፉት ሁለት አመታት ያሳኳቸውን ዋና ዋና ተግባራት የሚቀርቡበት፣ በዕቅድ ያስቀመጧቸውን ግቦች ለማሳካት ምን እየሰሩ እንደሆነ የሚያሳዩበት መደረክ እንደሚሆን የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር ሚኒስትር ክብርት ወ/ሮ ጫልቱ ሳኒ ተናግረዋል፡፡

ክብርት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ ከህዳር 6-10 2018 ዓ.ም በአፋር ክልል በሰመራ ሎጊያ ከተማ “የከተሞች ዕድገት ለኢትዮጵያ ልህቀት” በሚል መሪ ቃል የሚካሄደውን 10ኛውን የኢትዮጵያ ከተሞች ፎረም በማስመልከት መግለጫ ተሰጥተዋል።

ክብርት ሚኒስትር በመግለጫቸው የከተሞች ልማት በአስተማማኝ ሁኔታ የሚረጋገጠውና ለሀገር አቀፍ ዕድገት የሚጠበቅባቸዉን አስተዋጽኦ በአግባቡ ማበርከት የሚያስችላቸዉ አቅም የሚፈጠረው በዋናነት በከተማ ነዋሪው ህዝብ ተሳትፎ እና ትብብር ነው ብለዋል።

በመሆኑም በከተማና መሰረተ ልማት ዘርፍ አጀንዳዎች ዙሪያ ጠንካራ መሰረት ያለዉ የከተማ ህዝብ ንቅናቄና ተጠቃሚነት ለመፍጠር እንዲቻል በየሁለት ዓመቱ “የኢትዮጵያ ከተሞች ፎረም” እንዲዘጋጅ ተወስኖ አስከ 9ኛው እየተከበረ የቀጠለ ሲሆን በ2018 ዓ.ም 10ኛውን የኢትዮጵያ ከተሞች ፎረም በአፋር ክልላዊ መንግስት ሰመራ ሎጊያ ከተማ ይካሄዳል፡፡

ከዚህ ቀደም በዘጠኝ ዙሮች የተካሄዱት የከተሞች ፎረም ዝግጅቶች የታለመላቸውን አላማ ከማሳካት አንፃር ቀላል የማይባል አስተዋጽኦ ማበረከታቸውን ገልጸዋል፡፡ በተለይ በየአመቱ መሻሻሎችን በማሳየት የዘርፉን ውጤታማነት ለማረጋገጥ በሚያስችል የትኩረት አቅጣጫዎች ላይ በማተኮር ዝግጅቶች በመካሄዳቸው በከተማ ልማት ዘርፉ ላይ እየተደመረ የሚሄድ ውጤት መታየት መቻሉን ክብርት ሚኒስትር ተናግረዋል፡፡

ፎረሙ በከተሞች መካከል የእርስ በርስ ቅርርብና ትውውቅ እንዲጎለብት፣ በተመራማሪዎችና በዘርፉ ባሉ ተዋናዮች መካካል ውይይት በማድረግ በከተማ ዘርፍም ይሁን በሙሁራኑ ላይ ግንዛቤ እንዲፈጠር፣ ጤናማ ውድድር እንዲኖር፣ የልማት ሃይሎች እንዲበረታቱ፣ መልካም ተሞክሮዎች እንዲስፋፉ በማድርግ በከተሞች መካካል ተቀራራቢ የሆነ ልማትና እድገትን በማምጣት ከተሞችን የልማት፣ የዲሞክራሲና የመልካም አስተዳደር ማእከል ለማድረግ እድል ይፈጥራል ብለዋል፡፡

ከዚህ ጋር በተያያዘ በከተሞች ልማትን በማፋጠን ያደጉና የተለወጡ ከተሞችን የመፍጠር ስራ ወቅቱ ከሚጠይቀው የአስተሳሰብና ትግበራ ሁኔታዎች ጋር የሚራመድ በመሆኑ የ10ኛው ዙር ዝግጅት ከተሞችን በተሻለ ደረጃ መለወጥ (transform) ለማድረግ በሚያስችል የእውቀት ሽግግር ላይ ትኩረት ተደርጎ የሚሰራበት ይሆናል ሲሉ ክብርት ሚኒስትር ጫልቱ ገልጸዋል፡፡

በመረሀ ግብሩ 150 ከተሞች እና ከ10 በላይ ድርጅቶች እንደሚሳተፉ ይጠበቃል፡፡

Posted in: ዜና