መጋቢት 4, 2026
አዲስ አበባ፣ የካቲት 20/2018 ዓ.ም፣ (ከመልሚ)
ሚኒስቴር መ/ቤታችን በዘርፉ ያለውን የዕውቀት ሽግግር ለማጠናከር፣ አዳዲስ የፈጠራ ሀሳቦችን ለማፍለቅና በሪፎርም ስራዎቻችን ላይ የጋራ ግንዛቤ ለመፍጠር “አውደ-ሀሳብ በከተማና መሠረተ-ልማት” በሚል ስያሜ በየወሩ የውይይት መድረክ ማድረግ ጀምሯል።
ለሁለተኛ ጊዜ በሚካሄደው መድረክም በዘርፉ የሚታዩ ውስብስብ ችግሮችን በሣይንሳዊ እና በተግባራዊ ዕውቀት ለመፍታት የሚያስችሉ የፖሊሲ ግብዓቶች የሚሰበሰብበት ስለሆነ ትኩረት ያደረገውም ከቤት ልማትና አቅርቦት ስራዎቻችን ጋር በተያያዘ “በቤት ልማት የትብብር እና የውድድር ሞዴል” ርዕሰ-ጉዳይ ላይ ያተኮረ ነው፡፡
ማብራሪያውን የሰጡት የቤቶችና ከተማ ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክብርት ወ/ሮ ሔለን ደበበ ሲሆኑ የውይይት መድረኩን የመሩት ደግሞ የቤቶች ልማት መሪ ስራ አስፈጻሚው አቶ ፀጋዬ ሞሼ ናቸው፡፡ በውይይት መድረኩ ላይም የሚኒስቴር መ/ቤቱ ከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች፤ የተጠሪ ተቋማት ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች፤ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የቤቶች ልማት ቢሮ ኃላፊዎች፣ የሪልስቴት አልሚዎች፤ ሌሎች ባለድርሻ አካላት እና ጥሪ የተደረገላቸው ዕንግዶች ተሳትፈዋል፡፡
ለክብርት ወ/ሮ ሄለን የቀረቡላቸው ጥያቄዎች በቅርቡ የጸደቀውን የቤት ልማት ፖሊሲ የተመለከቱ ሲሆኑ እነሱም፡- ትብብር ከቤት ልማት አንጻር እንዴት ይታያል? የትብብር ሞዴሉ በመንግስት እና በግሉ ዘርፍ እንዴት ይገለጻል? ወርቃማው ሚዛንስ የትኛው ነው? ዋና ዋና የፖሊሲ ጉዳዮችስ ምን ምን ናቸው? ቤት አገልግሎት ነው ወይስ አሴት? ፖሊሲው ስኬታማ ነው የምንለው ምን ውጤት ሲገኝ ነው? የሚሉና ሌሎች ከቤት ልማት ፖሊሲው ጋር ተያያዥነት ያላቸው ዝርዝር ጉዳዮችን የተመለከቱ ጥያቄዎች ናቸው፡፡
ክብርት ሚኒስትር ዴኤታ ወ/ሮ ሔለን ደበበ በሰጡት ምላሽ የመንግስትን ሚና በተመለከተ መንግስት ኢኮኖሚውን በበላይነት የመቆጣጠር ሳይሆን የገበያ ክፍተት ባለባቸው ቦታዎች እየገባ ክፍተቶችን መሙላትና ለግል ባለሀብቱ ምቹ መደላድልን ከመፍጠር ባሻገር የቤት ልማቱን ብቻውን የማልማት ፍላጎት እንደሌለውና በትብብር እና በውድድር መንፈስ ሚናውን መወጣት ነው ፍላጎቱ፤ ለዚህም ነው የመንግስትና የግል አጋርነት እንዲኖር ያስፈለገበት ዋናው ምክንያት በማለት ገልጸዋል፡፡
ወርቃማው ሚዛን የተባለውም በሁሉም ስርዓቶች ውስጥ የነበሩትን መልካም ነገሮች ወስዶ የተሻለ ስራን መስራት እንደሆነ እና ዋና ዋና የፖሊሲ ጉዳዮችን በተመለከተም በ8 የተከፈሉ መሆናቸውን በመግለጽ እነሱም ፡- የመሬት አቅርቦት፤ የፋይናንስ አቅርቦት፤ የቴክኖሎጂ ግብአት አቅርቦት፤ የመግዛት አቅም፤ የአልሚዎችን ሙሉ አቅም የመጠቀም፤ የገጠር ቤት ልማትን ማጠናከር፤ የቤት መረጃ አስተዳደር ሥርዓትን ማጠናከር፤ ጠንካራ የቤት ገበያ ሥርዓትን መገንባት የሚሉት መሆናቸውን በዝርዝር አብራርተዋል፡፡
ቤት አሴት ነው ወይስ አገልግሎት ተብሎ ለቀረበላቸው ጥያቄም ሲመልሱ የመደመር መንግስት ፍላጎት ቤት ከአሴትነት ወደ አገልግሎት እንዲቀየር ማድረግ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የፖሊሲው ውጤታማነት የሚለካው ምን ምን ጉዳዮችን አሟልቶ ሲገኝ ነው ተብሎ ለቀረበላቸው ጥያቄም ሲመልሱ አራት ነገሮችን አሟልቶ ሲገኝ መሆኑን በመግለጽ እነሱም፡- የተጣጣመ የቤት ፍላጎትና አቅርቦት ሲኖር፤ የተሻሻለና አስተማማኝ የቤት ገበያ ስርዓት ሲኖር፤ የተሻሻሉ የገጠር ቤቶች ሲገነቡ እና ተቋማዊ አቅም ሲገነባ እና የዲጂታል ስርዓት ዕውን ሲሆን የሚሉትን ነጥቦች አስቀምጠዋል፡፡
በመጨረሻም ከተወያዮች ፖሊሲውን ወደ መሬት ለማውረድ በሚዘጋጁ የተለያዩ ሠነዶች ላይ ሊካተቱ የሚገባቸው በርካታ ሀሳብና አስተያየቶች እንዲሁም የግልጽነት ጥያቄዎች ቀርበው የተብራራ ገለጻና ማብራሪያ ከተሰጠ በኋላ በሰጡት የማጠቃለያ አስተያየት ተሳታፊዎች ያነሳችኋቸው ሀሳቦችና የሰጣችኋቸው ግብኣቶች የዜጎቻችንን ችግር በጋራ ፈትተን ዜጎች ተደስተው የሚኖሩባትን ሀገር ለመፍጠር የሚያስችሉ ናቸው በማለት ተሳታፊዎች ለነበራቸው የነቃ ተሳትፎ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡